ቀጥታ፡

አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት የተሻለች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል ምክክር እያደረግን ነው 

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት የተሻለች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል ምክክር እያደረግን ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ምክክር የሚደረግባቸውን ስምንት አጀንዳዎች መለየቱ ይታወሳል።  

በአጀንዳዎቹ ላይ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በተገኙበት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ተመካካሪዎች፣ ሂደቱ በግልጽነትና በሃላፊነት ስሜት እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡

ለሀገር የሚበጁ አጀንዳዎች ላይ በሰለጠነ መንገድ ምክክር እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ከተመካካሪዎቹ መካከል አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ለምክክሩ አካታች በሆነ መንገድ ተመካካሪዎቹን መምረጡን በአካል በመሳተፍ አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ከጣልቃ ገብነት የጸዳ፣ ዜጎች በራሳቸው ፍላጎትና ባለቤትነት የሚመራ በመሆኑ ለሌሎች ሀገራትም ትልቅ አርዓያ የሚሆን ልዩ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል።

አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ምክክር እንዲደረግ ሊቃውንት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ዜጎች ለዘመናት ሲጠይቁት የነበረ ጉዳይ መሆኑን አስታውሰዋል። 

አሁን የጀመርነው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለዚያ ጥያቄ መልስ የሰጠ ነው ያሉት አርክቴክት ዮሐንስ፤ ሁሉም በጋራ ሆኖ ልዩነቱን ተመካክሮ መፍትሔ የሚያበጅበት ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል ብለዋል። 

ምክክሩ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደፊት ልዩነቶችን ለመፍታት ኃይል ሳይሆን የሰለጠነ አካሄድ መፍትሄ እንዲሆን መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

ሌላኛው ተመካካሪ መምህር ሞገስ ፍሥሓ በሰጡት አስተያየት፣ ሂደቱ እጅግ በሚያበረታታ መልኩ እየቀጠለ መሆኑን በመጥቀስ፤ መድረኩ በምክክር አዲሷን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ታላቅ ዕድል የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል። 

ምክክር አንዱ የሌላውን ሐሳብ በማዳመጥ መግባባት መፍጠር ነው ያሉት ሌላኛው ተመካካሪ ናስር አብደላ፤ በምክክር ጉባኤውም ሁሉም ተመካካሪ ሐሳቡን በነፃነት እየገለጸና እየመከረ ነው ብለዋል።   

ሌላኛዋ ተመካካሪ ዝማማ አቡሃይ በበኩላቸው፣ በምክክሩ ሀገርን የሚያሻግር መፍትሔ እንዲመጣ ሀገርና ሕዝብ አደራ ጥሎብናል ብለው ይህንን ታሪካዊ አደራ በብቃት ለመወጣት ሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 

ተመካካሪ ሊዲያ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ በአጀንዳዎች ላይ ሐሳባችንን በነፃነት በማቅረብ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለን ያሰብነውን መፍትሔ ለማምጣት እየተጋን ነው ብለዋል፡፡

በምክክሩ ሂደት ባለቸው ተሳትፎም የራሳቸውን ሐሳብ ከማካፈል ባለፈ፣ ከሌሎች ተመካካሪዎች የሚነሱ ሃሳቦችን በማዳመጥ ጥሩ የምክክር ጊዜ እያሳለፉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ተመካካሪ ሲሳይ ዘለቀ በበኩላቸው፤ የምክክር መድረኩ የሀገሪቱን የጋራ የወደፊት ዕድል ለመወሰን ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ገልጸዋል። 

ሌላኛው ተመካካሪ ባንዲራ በላቸው በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ምክክር አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት የተሻለችና የጸናች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል ታላቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም