ቀጥታ፡

በዞኑ የመኸር አዝመራን ውጤታማ  ለማድረግ ለኩታ ገጠም እርሻና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትኩረት ተሰጥቷል

ወልቂጤ ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን የመኸር አዝመራን ውጤታማ  ለማድረግ ለሰብል እንክብካቤ፣ ለኩታገጠም እርሻና ለግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ ፡፡

በዞኑ በአበሽጌ ወረዳ  የኩታ ገጠም የመኸር አዝመራ ልማት የመስክ ምልከታ ተደርጓል፡፡


 

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዞኑ የመኸር  ሰብልን  ውጤታማ ለማድረግ በ177 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም  የተለያዩ ሰብሎች ለምተዋል፡፡


 

በኩታ ገጠም እርሻውም በቆሎ፣ ማሽላ፣  ገብስ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ሩዝ እና  ጤፍ በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ለግብአት አቅርቦት፣  ለባለሙያ ድጋፍ፣ ለሰብል እንክብካቤና ለግብርና ቴክኖሎጂ  አጠቃቀም ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሱ ጁሃር በበኩላቸው፤  በወረዳው በዘንድሮው የመኸር ወቅት ግብአትና የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን በመጠቀም አርሶ አደሮች  ምርታማነታቸውን  እንዲያሳድጉ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡


 

የአበሽጌ ወረዳ የአቡኮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዘሪሁን ቱሉ፤  የግብርና ባለሙያዎች የሚያደርጉላቸውን ድጋፍ ተጠቅመው አራት ሄክታር  ኩታ ገጠም መሬታቸውን በበቆሎ ማልማታቸውን ተናግረዋል።

የበቆሎ  ሰብሉን  ከአረም እና ከበሽታ በመከላከል  የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

አርሶአደር ሃይሉ ዴሲሳ በበኩላቸው፤  ሶስት ሄክታር  የበቆሎ ማሳቸውን እየተንከባከቡ በመሆናቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።

ከሌሎች  አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በ30 ሄክታር መሬት ጤፍን በኩታ ገጠም  በማልማት እንክብካቤ  እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  አርሶ አደር ዳዊት አሰፋ ናቸው።

ምርታማነታቸውን ለማረጋገጥም የተሻሻለ  የጤፍ ዝርያን  መጠቀማቸውንና የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገላቸው  መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም