ቀጥታ፡

ደም በመለገስ የወገኖቻችንን ህይወት ለመታደግ ሀላፊነታችንን እየተወጣን ነው 

ዲላ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ደም በመለገስ  የወገኖችን ህይወት ለመታደግ  ሰብአዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን በዲላ ከተማ በጎ ፈቃደኛ የህብረተሰብ ክፍሎች  ገለጹ። 

በከተማው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆነ በአንድ ጀንበር 100 ዩኒት ደም የማሰባሰብ ዘመቻ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ እየተካሄደ ነው፡፡

ደም ለጋሾቹም በበጎ ተግባራቸው የሰው ህይወት በመታደጋቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል በአሽከርካሪነት ሙያ የተሰማሩት አቶ ከድር አሊ፤ የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎችን ለማከም በሚደረግ ጥረት የደም እጦት ጫና ሲፈጥር ማስተዋላቸውን አንስተዋል።


 

የተመለከቱትን  ችግር ለመቅረፍ  በሚደረገው ጥረት በዛሬው ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።

ደም መለገስ እናቶች በወሊድ ወቅት የሚገጥማቸውን የደም እጥረት ለመሸፈን ድርሻው የጎላ መሆኑን ያነሳቸው ደግሞ ወጣት ናርዶስ ተሾመ ናት።


 

በዘመቻው በመሳተፍ ደሟን በመለገሷ የተለየ ደስታ እንደፈጠረባት ተናግራ በቀጣይም በሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በመሳተፍ የክረምት ወራትን በበጎ ተግባራት ለማሳለፍ እየሰራች መሆኑን ገልጻለች።

አቶ ታምራት አሰፋ በበኩላቸው፤ ደም መለገስ በቀላሉ ልናደርገው የምንችለው በጎ ተግባር በመሆኑ  በቀጣይም አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል።

የዶርቃ በጎ አድራጎት ህብረት ሰብሳቢ ወጣት እሱባለው ገብረሕይወት በበኩሉ፤ ህብረቱ ከ100 በላይ የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በስሩ ይዞ በከተማው በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሷል።


 

በበጎ ፈቃድ ደም መለገስ የመንፈስ እርካታን የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሶ በተለይ የደም ልገሳ ሕይወት የማዳን ተግባር በመሆኑ ለየት ያደርገዋል ብሏል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መላኩ አየለ በበኩላቸው፤ በከተማው በክረምት በጎ ፈቃድ ከ143 ዩኒት በላይ ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን ጠቅሰዋል።


 

በዛሬው ቀንም ወጣቱን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር 100 ዩኒት ደም የማሰባሰብ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በከተማው የደም ልገሳን ጨምሮ በ19 ዘርፎች ከ98 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም