በዞኑ እየተካሔደ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ እየተካሔደ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ጎንደር፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በማእከላዊ ጎንደር ዞን የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የዞኑ ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው የ2018 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2019 ዓ.ም እቅድ ትውውቅ መድረክ በጎንደር ከተማ ዛሬ ተካሒዷል።
የመምሪያ ኃላፊው አቶ ገድፍ ጌትነት በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የለውጡ መንግስት አሻራ የሆነው የኮሪደር ልማት ከተሞችን በማዘመን ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑ ስር በሚገኙ በአራት የከተማ አስተዳደሮችና በዘጠኝ መሪ ማዘጋጃ ቤት ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
ለኮሪደር ልማት ስራው ህብረተሰቡ ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ በማድረግ ለልማት ያለውን ቁርጠኝነት ማረጋገጡን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ፤በ2019 በጀት ዓመት የልማት ስራውን ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋፋት ስራ ትኩረት እንደሚሰጠው አንስተዋል።
ከተሞችን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የዞኑ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋሲል ሠንደቁ ናቸው።
ይህም ከተሞቹን በማዘመን ለነዋሪዎች፣ ለጎብኝዎችና ለንግድ የተመቹ ከማድረግ ባለፈ የክልሉን ገጽታ ለመገንባት ተደማሪ አቅም እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
በዞኑ የአንባ ጊዮርጊስ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሠረተ ልማት ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ዲያቆን ወልዴ ባዘዘው እንደገለጹት ፤ የኮሪደር ልማቱ የማሕበረሰቡን አኗኗር ለማዘመን የሚያስችል ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማት ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ደረጃውን የጠበቀ የሳይክልና የእግረኛ መንገድ መገንባት መቻሉን አመልክተዋል።
ሌላው የጎንደር ዙሪያ ወረዳ የማክሰኝት መሪ ማዘጋጃ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉአለም ሙጨ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማት ስራው ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመትም የኮሪደር ልማት ስራውን አጠናክሮ በማስቀጠል የከተማዋን እድገት ለማፋጠንና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ በዞኑ የሚገኙ የከተማ አስተዳደሮች፣የወረዳ ከተማ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።