ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ መሠረት የሚጥል ታሪካዊ አጋጣሚ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የዘመናት ቁርሾና አለመግባባቶችን በመፍታት ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ መሠረት የሚጥል ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች በተገኙበት ዋናው የምክክር ጉባኤ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ተጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ማስጀመሪያ ላይ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይል እርምጃ የመቋጨት ባህል ያለበት ሆኖ መቆየቱን ታሪክ ያስረዳል።

ይህም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ከማረጋገጥ፣ ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ እንዲሁም የውስጥ ሰላም ከማረጋገጥ አኳያ አሉታዊ ጥላ ያጠላበት ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል።

በዚህም የሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን ''ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ መክፈት እንደቻለ አብራርተዋል። 

ኢትዮጵያውያን በምክክር ሂደቱ መግባባትን በመፍጠር ለአንድ የሀገር አንድነት ዓላማ በመቆም፤ ለፈተናዎች የማይበገርና ታሪካዊ ሴራዎችን የምትመክት ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው፤ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ኢትዮጵያውያን በማያግባቡ ጉዳዮች ላይ ተገናኝተው የሚመክሩበት ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል። 

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዞ የሚያቀና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ምቹ ምኅዳር የፈጠረ መሆኑንም በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ አብስረዋል። 

የዋናው የምክክር ጉባኤ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎችም የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን መፍትሔ ለማምጣት በግልፅነትና በታማኝነት ሐሳባቸውን የሚያካፍሉበት ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል። 

በዚህም ከሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ሕዝብ የወከላቸው ተመካካሪዎች በንዑስ ቡድኖች በመከፋፈል በተመደቡበት አጀንዳ ላይ እየተመካከሩ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት መምህርና ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ ልማት ከፍ ለማድረግና በአፍሪካ ቀንድ ያላትን አህጉራዊ ተጽዕኖ ለማረጋገጥ በሀገር ግንባታ ዙሪያ የጋራ መግባባት መፍጠር ወሳኝ ነው። 

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤም ለዘመናት የዘለቁ ሀገራዊ ችግሮችን መፍትሔ በመስጠት ረገድ ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል አስገንዝበዋል። 

ለዘመናት የዘለቁ የቁርሾና የልዩነት ማነቆዎችን በምክክር ለመሻገር የተሰነዱ ስምንት ዐበይት አጀንዳዎችም ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለማነፅ መሠረት መሆናቸውን አንስተዋል። 

የምክክር ሐሳቦቹ ከሕዝቡ የልብ ትርታ ተነስተው በባለቤትነት መንፈስ የሚመሩ በመሆናቸው፣ የምክክር ሂደቱ ፍሬያማና ኢትዮጵያን ለነገ የተሻለች ሀገር አድርጎ ለማዋቀር የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

የታሪክ ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በግጭትና በአለመግባባት የምትገነባ ሀገር እንደሌለች በመጥቀስ፣ ምክክር የጋራ መግባባት ላይ ለማድረስ የሚያግዝ የሀገር ግንባታ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምክክርም የተለያየ ሐሳቦችን በአንድ ጣሪያ ሥር በማሰባሰብ፣ ማሸነፍና በመሸነፍ የዘለቀውን የዘመናት አለመግባባትና የታሪክ ስብራት ለመጠገን የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል። 

ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤም ልዩነቶችን ከማስተናገድ ባለፈ፣ የተለያዩ ድምፆች የሚደመጡበትና የሀገር ግንባታ አቅጣጫ በጋራ የሚቀመጥበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ እንደሚሉትም፤ ምክክር የጋራ አሸናፊነትን የሚያቀዳጅ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ የጋራ መድረክ ነው። 

በምክክር አሸናፊና ተሸናፊ እንደሌለና አሸናፊዋ ሀገር ናት ያሉት አማካሪው፤ ምክክር የተለያዩ አመለካከቶችን በማቀራረብ የዛሬን ልዩነቶች ወደ መግባባት የሚያሻግር የነገን ጠንካራ ሀገር መገንቢያ ድልድይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም