ቀጥታ፡

በከተማው እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ልጆች ሁሉ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው 

ዲላ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በዲላ ከተማ በመጪው የትምህርት ዘመን እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ልጆች ሁሉ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ከወዲሁ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የከተማው ትምህርት መምሪያ ገለጸ።

በከተማው የትምህርት ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።


 

የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ታሪኩ በየነ በወቅቱ እንዳሉት፤ በመጪው የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶችን ለተማሪዎች ምቹ በማድረግ የትምህርት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ከወዲሁ እየተሰራ ነው።

በተለይ የተማሪዎችን ውጤት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃና መሰረተ ልማት በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ጥረት ይጠናከራል ብለዋል።

የተማሪዎች ቅበላን በአግባቡ ከማከናወን ባለፈ የመምህራንን አቅም ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በከተማው ህብረተሰቡንና አጋር አካላትን በማስተባበር በትምህርት ልማት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ያነሱት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ሆርዶፋ ናቸው።


 

በተለይ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከ80 በላይ መማሪያ ክፍሎችን በመገንባት ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቁመው ይህም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በትምህርት ልማት የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል በመጪው የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት የተጠናከረ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመጪው የትምህርት ዘመን ከ41 ሺህ 528 በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ልጆች ሁሉ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ለማድረግ ከወዲሁ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።


 

በዲላ ከተማ የቆፌ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አብነት ሽፈራ በበኩላቸው፤ በትምህርት ቤቱ በመንግስት፣ በህብረተሰብ ተሳትፎና በአጋር አካላት ድጋፍ የተገነቡ 12 መማሪያ ክፍሎች የትምህርት ቤቱን ደረጃ ማሻሻላቸውን ጠቅሰዋል።

በመጪው የትምህርት ዘመን የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም