ህገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል መኖር የማያስችል ስርዓት አልበኝነት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ህገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል መኖር የማያስችል ስርዓት አልበኝነት ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2018(ኢዜአ)፦ ህገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል መኖር የማያስችል ስርዓት አልበኝነት መፍጠሩን የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሀፍቱ ኪሮስ ገለጹ።
በአሁኑ ወቅት ህገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የክልሉን ወጣቶች ለሌላ አሳልፎ መሸጥን ጨምሮ የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ በማካሄድ ከፍተኛ ግፍና መከራ እያደረሰ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ሀፍቱ ኪሮስ በወቅታዊ የትግራይ ሁኔታ ላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በክልሉ ህግና ስርዓት በመፍረሱ ምክንያት የህዝቡ ሰላምና ደህንነት ለአደጋ መጋለጡን አንስተዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የትግራይ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት እንዲያገኝና ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ማስቻሉን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ግን ህገ ወጡ የሕወሓት ቡድን የክልሉን ሕዝብ አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የሰላም ስምምነቱን በማፍረስና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን እየፈፀመ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ይህ ህገ ወጥ ቡድን በፈጠረው ስርዓት አልበኝነት በክልሉ ወጣቶች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት እየፈጸመና በግዳጅ አፈሳ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
የህዝቡን ሰላም እና መረጋጋት ለመመለስ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሊተገበር እንደሚገባም ነው አቶ ሀፍቱ ኪሮስ የተናገሩት።
አሁን በትግራይ ክልል ውስጥ የሚስተዋለው አፈሳ እና ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት ወጣቶች አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ህዝቡ በተደራጀ መንገድ የራሱን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር መቆም እንዳለበትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ መልክ መያዝ እንደሚገባው ጠቁመዋል።
ህገወጡ የሕወሓት ቡድን በክልሉ እየፈጠረ ያለው ችግር አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስ፣ ህዝቡ በራሱ አቅም ተደራጅቶ ሰላሙንና ደህንነቱን ማስጠበቅ እንደሚገባውና ህገ ወጥ ቡድኑ እየፈጠረ ያለው ቀውስ በአፋጣኝ መፍትሄ ማግኘት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት በክልሉ ህግና ስርዓትን የማስከበር እንዲሁም የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ መሥራት እንዳለበትም አንስተዋል፡፡