ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ የህብረተሰቡ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ ነው

 ባህር ዳር፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ  የህብረተሰቡ  ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ  ሴቶች ፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ  ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ዝና ጌታቸው በባህር ዳር ከተማ በተካሄደ የደም ማሰባሰብ ስነስርአት ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ በክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት 30 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

እስካሁን ከ5ሺህ 400 በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ተናግረዋል።


 

በዛሬው እለትም በሃገር አቀፍ ደረጃ የታቀደውን የአንድ ጀንበር 10 ሺህ ዩኒት ደም የመሰብሰብ ግብ ለማሳካት በክልሉ  እስከ ቀበሌ ድረስ የደም ልገሳ መርሐግብር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የደም ልገሳ ፕሮግራሙ የወላድ እናቶችን እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ደም የሚያስፈልጋቸው  ወገኖችን ህይወት መታደግን አላማ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ የደም ልገሳ ተግባርን ከዘመቻ ስራ ባለፈ  የህብረተሰቡ  ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በትኩረት እየተሰራ  መሆኑን አስታውቀዋል።

ደም  ከለገሱ ዜጎች መካከል  አቶ ሙሉሰው ጌጡ እንደገለጹት፤ ደም በመለገስ  በደም እጦት የሚቸገሩ ህሙማንን ህይወት  መታደግ ይገባል ። 


 

በበጎ ፈቃድ ደም በመለገስ ሌሎችን ከመርዳት ባለፈ የህሊና እርካታ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል። 

ዛሬ ደም ሲለግሱ ለ2ኛ ጊዜያቸው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሙሉሰው፤ ተግባሩን ለማስቀጠል ከመወሰናቸው ባለፈ ሌሎችም አርአያነታቸውን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወይዘሮ ውዴ እምቢያለ በበኩላቸው፤ ደም በመለገስ በደም እጦት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች በመድረስ ለወገን አለኝታነታቸውን ለማሳየት መገኘታቸውን ጠቁመዋል።


 

ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉትን የደም ልገሳ  ተግባር አጠናክረው  እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።

በክልሉ የዛሬው የደም ልገሳ ዘመቻም በሁሉም ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች ሁሉንም ህብረተሰብ በማሳተፍ እየተካሄደ መሆኑን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም