በወረዳው የቅመማ ቅመም ልማትን ለማሻሻል እየተካሄደ ባለው የተቀናጀ ስራ ውጤት እየተገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወረዳው የቅመማ ቅመም ልማትን ለማሻሻል እየተካሄደ ባለው የተቀናጀ ስራ ውጤት እየተገኘ ነው
ሚዛን አማን፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሸካ ዞን የኪ ወረዳ የአርሶ አደሩን የቅመማ ቅመም ልማት ለማሻሻል ከግብርና ምርምር ማእከላት ጋር እየተካሄደ ባለው የተቀናጀ ስራ ውጤት እየተገኘ መሆኑ ተገለጸ።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ዳዊት ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ወረዳው ለቅመማ ቅመም ያለውን ምቹ ሥነ-ምህዳርና ከፍተኛ የገበያ ተፈላጊነት በመጠቀም በዘርፉ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው።
በዚህም በወረዳው የአርሶ አደሩን ቅመማ ቅመም ልማት ለማሻሻል ከግብርና ምርምር ማእከላት ጋር እየተካሄደ ባለው የተቀናጀ ስራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገ ጥረት ልማቱ ከ8ሺ200 ሄክታር በላይ መሬት ላይ መስፋፋቱን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የቅመማ ቅመም ዝርያዎችን በኩታ ገጠም እንዲያለማ በመደረጉ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉንም አመልክተዋል ።
በዚህም በተለይ የቁንዶ በርበሬ እና እርድ አምራች አርሶ አደሮች የገቢ ምንጫቸው ማደጉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የልማት ሂደቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ዘመናዊ የምርት ማቀነባበሪያ ማሽኖች ለማቅረብ በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ቅመማ ቅመምን በማልማት ምርታቸውን ማሳደጋቸውን የገለጹት ደግሞ የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ተስፋሁን ናቸው።
በወረዳው የእርድና የቁንዶ በርበሬ ልማትን በማስፋፋት አርሶ አደሩ ከምርቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርአት ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።
የወረዳው አርሶ አደሮች በበኩላቸው የኩታ ገጠም የቅመማ ቅመም የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም ምርታማነታቸውን ማሳደጋቸውን አንስተዋል።
በወረዳው የኅብረት ፍሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የሱፍ መሐመድና አርሶ አደር ይመር አበጋዝ በቁንዶ በርበሬ ልማት ተሰማርተው ከምርት ሽያጭ ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደር አሊ ሞላ እና አወል እንድሪስ በበኩላቸው በእርድ ልማት ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምርቱ በገበያ ላይ ተፈላጊ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።
የእርድ ልማቱን በኩታገጠም መስራታቸው ለእንክብካቤና ለምርት አሰባሰብ ሂደቱ ምቹ መሆኑን የተናገሩት አርሶ አደሮቹ በቀጣይም የምርት ዝግጅት ሂደቱን በዘመናዊ ማሽን ለማካሄድ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።