ቀጥታ፡

ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ መሳተፋቸው የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጎልበት ያግዛል

ደብረብርሃን ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ መሳተፋቸው የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጎልበት ያግዛል ሲሉ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ገለጹ።

ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ያሳተፈው የክረምት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ -ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ጠባሴ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር ዛሬ ተጀምሯል።

ወጣቶቹ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና  መሰረት የሚጥሉ በመሆናቸው ተሳታፊነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ መካከል ከጌዲዮ ዞን ዲላ ከተማ የመጣችው ወጣት ትንሳኤ ትዕዛዙ እንደገለጸችው፤ የአገራችን ከፍታ የሚረጋገጠው አንድነታችን በመጠበቅ ለጋራ አላማ በአንድነት ስንቆም ነው።

የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሁሉም አካባቢዎች የተሰባሰቡ ወጣቶች የአረንጓዴ አሻራቸውን በማስቀመጥ የሀገር አንድነትና እድገትን ለማጽናት የምንሰራበት ነው ስትል አንስታለች።

ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የመጣው ወጣት አላዛር ታሪኩ በበኩሉ ፤በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  በጋራ የሚተከሉት  ችግኞች በህዝቦች መካከል መቀራረብን፣ አብሮነትንና አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ናቸው ብሏል።


 

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ ስራ ወጣቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባሀል፣ ወግና እሴትን እንዲረዳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተናገረው።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የተከልናቸው ችግኞች አገራዊ አንድነትና ትብብርን ለማጠናከር የሚያግዙ ናቸው ያለችው ደግሞ ከአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ከሚሴ ከተማ የመጣችው ሰዓዳ ኢንድሪስ ናት።

በተለይም በህዝቦች መካከል በተሳሳተ ትርክትን በማጥፋት ዘላቂ ፍቅርን፣ ሰላምና ልማትን ለማጎልበት የሚያስችል ነው ስትል  ተናግራለች።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በከተማዋ ተስማሚ የአየር ንብረትና ስነ ምህዳር ለመጠበቅ ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

በተለይም እየተስፋፋ የመጣው የኢንዱስትሪ ልማትና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ይበልጥ ለማሳደግ የላቀ ድርሻ እንደሚኖረው ነው የገለጹት። 

የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ለታለመለት ግብ በማብቃት ከተማዋን ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች የተመቸች ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ መሳተፋቸው አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።

የደብረ በርሃን ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ መርሻ አይሳነው በበኩላቸው፤ በተያዘው የክረምት ወቅት ዘጠኝ ነጥብ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የደን፣ የውበትና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚሰጡ ችግኞች እየተተከሉ ነው ብለዋል።

በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከሁለት ሺህ 300  ሄክታር  መሬት በላይ ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ባለፉት ዓመታት የለሙ አካባቢዎች አሁን ላይ ጥቅም መስጠት እንደጀመሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም