በዞኑ የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ለንብ ማነብ ስራ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ለንብ ማነብ ስራ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል
፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና እንክብካቤ ላይ በተከናወኑ ተግባራት የደንና የአፈር ለምነት በማሳደጉ ለንብ ማነብ ስራቸው ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አርሶ አደሮች ገለጹ።
በሐረርጌ ዞን በሸነን ዱጎ ወረዳ በማር ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንዳሉት፣ ባለፉት አመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች የደን መጠን እንዲጨምርና ምንጮች እንዲጎለብቱ አድርገዋል።
ይህም ከመደበኛ የግብርና ስራቸው በተጓዳኝ ለንብ ማነብ ስራ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
በወረዳው የመደ ጃለላ ቀበሌ አርሶ አደር የሆኑት አህመድ አብዱሌ ፤ ከአካባቢው ስምንት አርሶ አደሮች ጋር በማህበር በመደራጀት የማር ልማት ስራ ላይ መሰማራታቸውን ይገልፃሉ።
በአሁኑ ወቅትም 24 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች እንዳሏቸው አመልክተው በዘርፉ በተሻለ መንገድ ስኬታማ ስራዎችን ለማከናወንም በግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትልና እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደር መሐመድ አህመድ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በንብ ማነብ ሥራ በመሰማራት የማር ልማት ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከግብርና ባለሙያዎች በተደረገላቸው ድጋፍና ክትትል ከንብ ማነብ ሥራ ጎን ለጎን በወተት ላም እርባታ ላይ በመሰማራት ኑሯቸውን ለማሻሻል እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
የመደ ጃለላ ቀበሌ ምክትል አስተዳዳሪ ወይዘሮ ፀሐይ እንግዳ እንዳሉት፤ ባለፉት አመታት የተካሔደው የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ለንብ ማነብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በዋናነትም የደኖች መበራከትና የምንጮች መጎልበት በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች በተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎች እንዲሳተፉ መነቃቃት የፈጠረ ነው ብለዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች ከመደበኛ የግብርና ስራቸው በተጓዳኝ በንብ ማነብ ስራ ላይ እንዲሰማሩና ውጤታማ እንዲሆኑ የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት የማር ልማት ባለሙያ አቶ ከድር አደም እንዳሉት፤ በዞኑ ተግባራዊ የተደረገው የማር ልማት ኢኒሼቲቭ የምርታማነት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ30ሺ በላይ ዘመናዊ ቀፎዎች ለአርሶ አደሩ የተሰራጨ ሲሆን ከ 4 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት መገኘቱን አመልክተዋል።
በዚህ ዓመት የተገኘው ምርት መጠን ባለፈው ዓመት ከተገኘው ጋር ሲነፃፀር ከ500 ቶን በላይ ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል፡
በአዲሱ በጀት ዓመትም የምርት መጠኑን በእጥፍ ለማሳደግ ከ60 ሺህ በላይ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በዞኑ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ጋር በተያያዘ ለንብ ማነብ ስራ አመቺ ሁኔታ መፈጠሩን የገለፁት ባለሙያው ከ150ሺ በላይ አርሶ አደሮችም በግልና በማህበር ተደራጅተው በንብ ማነብ ስራ ላይ መሳተፋቸውን አመልክተዋል።