በነቀምቴ ከተማ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ ቅድመ ጥንቃቄ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴ ከተማ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ ቅድመ ጥንቃቄ ተደርጓል
ነቀምቴ፤ ሀምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ማከናወኑን አስታወቀ።
የከተማው ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሀላፊ ረጋሳ ሞሲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የክረምቱን መግባት ተከትሎ የከተማው ውሀ ማፋሰሻዎች በቆሻሻ በመዘጋት ለአደጋ እንዳያጋልጡ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ሰፊ የማፅዳት ስራ ተከናውኗል።
የውሃ ማፋሰሻ ቦዮችን የማጽዳት ተግባር ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተያያዘም በጎርፍ ሳቢያ ሊከሰት የሚችል የመሬት መንሸራተትና የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
ህብረተሰቡም በአካባቢ ፅዳትና ጥበቃ ስራዎች ላይ በንቃትና በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፍ ተከታታይ የህዝብ ንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በከተማው የኬጀማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ማቲያስ ሁንዴሳ በበኩላቸው በከተማው በክረምት ወቀት ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል ዘንድሮ በተጀመረው የፅዳት ስራ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በቆሻሻ የተዘጉ የውሀ ማፋሰሻዎችን አስቀድሞ ማስከፈቱ ጎርፍ ወደ መኖሪያ ቤት በመግባት በንብረትና በሰው ህይወት ላይ ያደርስ የነበረውን ጉዳት ማስቀረት ማስቻሉን አመልክተዋል።
ሌላኛው የጨለለቂ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጥላሁን በቀለ በበኩላቸው፤ በከተማው እየተከናወነ ያለው የውሃ ማፋሰሻዎችን የማፅዳት ስራ ህብረተሰቡን ከጎርፍና ከተላላፊ በሽታዎች ለመጠበቅ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ሊከሰቱ የሚችሉ ድንገተኛ የአደጋ ስጋቶችን ለመቀነስ በየቀበሌው የሚሰጠው ተከታታይ ትምህርትና መረጃ ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅና ስራውን በስኬት እንዲያከናውን ትልቅ አቅም መፍጠሩን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።