የጅማ ዩኒቨርሲቲ የባዮጋዝ የምርምር ማዕከል ለአፈር ለምነት እና ለግብርና ምርታማነት እገዛ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የባዮጋዝ የምርምር ማዕከል ለአፈር ለምነት እና ለግብርና ምርታማነት እገዛ እያደረገ ነው
ሀምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፡- ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው የባዮጋዝ የምርምር ማዕከል ለአፈር ለምነት እና ለግብርና ምርታማነት እድገት እገዛ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማከናወን የግብርና ስራን በማዘመን እና በማስፋፋት ዙሪያ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑ ተመላክቷል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ኢንጂነር ኤፍሬም ዋቅጅራ ለኢዜአ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተገነባው የባዩ ጋዝ የምርምር ማዕከል ሀይልን ከማመንጨት በተጨማሪ የስልጠና አገልግሎት እየሰጠ ነው።
በዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ይጣል የነበረውን ተረፈ ምርት በመሰብሰብ ባዮ ጋዝ በማምረት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ማእከሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት የአፈር ለምነት ለመጠበቅና ለግብርና ምርታማነት እድገት እገዛ እንዲያደርግ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ዲን ሰለሞን ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የግብርና ስራዎችን ውጤታማ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በተለይም የምርምር ማዕከሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ ከማሰራጨት በተጨማሪ፣ ዩኒቨርሲቲው በ150 ሄክታር መሬት ላይ ለሚያከናውነው የግብርና ሥራ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመካኒካል ትምህርት ክፍል መምህርና የባዩ ጋዝ የምርምር ማዕከል ፕሮጀክት አስተባባሪ ሸዋንግዛው ወርቃገኘሁ የምርምር ማዕከሉ በዘርፉ ብቁ ባለሞያዎችን ለማፍራት የስልጠና ማዕከል ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በሁለተኛ ዲግሪ 18 ተማሪዎች በዘርፉ እየሰለጠኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የባዩ ጋዝ የምርምር ማዕከሉ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን በትብብር እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አስተባባሪው እንደ ሀገር ባዩ ጋዝን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ታዳሽ ኃይል ምህንድስና ተማሪ የሆኑት ኢየሩስ አንተነህ እና ቤተልሔም አባዲ፤ ባዮ ጋዝ እንዴት እንደሚመረትና ወደ ጠቃሚ ኃይል እንደሚቀየር በተግባር የተደገፈ በቂ እውቀት እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ህብረተሰቡን በተጨባጭ ሥራዎች ለማገልገል የሚያስችላቸውን የማጠናቀቂያ የጥናት ጽሑፍ እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛዉ ተማሪ ፊሊጶስ ከፈለኝ በዩኒቨርሲቲው በዘርፉ እያገኘ ያለው እውቀት በምርምር ማዕከሉ ውስጥ በሚሰሩ ተጨባጭ ስራዎች የተደገፈ መሆኑን ተናግሯል።
ተማሪው አክሎም በቀጣይ የኢትዮጵያን የባዩጋዝ ምርት አቅም ለማሳደግ እንደሚሰራ አመላክቷል።