ሀገራዊ ምክክሩ ለሁሉም የምትመችና የጸናች ሀገር ለመገንባት ፅኑ መሰረት የሚያኖር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለሁሉም የምትመችና የጸናች ሀገር ለመገንባት ፅኑ መሰረት የሚያኖር ነው
ጎንደር ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለሁሉም የምትመችና የጸናች ሀገር ለመገንባት ፅኑ መሰረት የሚያኖር መሆኑን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሁሉም የሀገሪቷ ክፍሎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ባሰባሰባቸው ስምንት አንኳር አጀንዳዎች ላይ በአዲስ አበባ የምክክር ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ከአራት ሺህ በላይ ጉባኤተኞች የተሳተፉበት መድረክ የኢትዮጵያን የቆዩ ችግሮች በመፍታትና ስብራቶችን በመጠገን ለሁሉም የምትመች ጠንካራ ሀገር የመገንባት ትልም ለማሳካት እየተሰራ ነው።
የጉባኤው መክፈቻ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በችግሮች ውስጥ እድሎች ያሉ በመሆኑ የምክክሩን ታሪካዊ እድል በመጠቀም የጸናችና ለዜጎቿ የምትመች ሀገር መገንባት አለብን ብለዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለሁሉም የምትመችና የጸናች ሀገር ለመገንባት ፅኑ መሰረት የሚያኖር መሆኑን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ቴዎድሮስ ተሰማ ፤ ኢትዮጵያዊያን ያለ ምንም ልዩነት እየተሳተፉበት ያለው ምክክር ለኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
ለኢትዮጵያ ከምክክር ውጭ የተሻለ መፍትሄ የሚያመጣ የለም የሚሉት አስተያየት ሰጪው ችግሮቻችንን በምክክር በመፍታት ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ሀገር መገንባት አለብን ብለዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ምስጋናው ደሴ፤ የምክክሩ ውጤት የሀገርን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት በመሆኑ ለስኬቱ ሁላችንም መትጋት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
የምክክር ትርፉ ብዙ መሆኑን አንስተው ከዋልታ ረገጥ እሳቤና ከግጭት አዙሪት በመውጣት ሀገር ለመገንባት በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ተማሪ ሳሙኤል ተስፋሁን፤ የምክክሩ ዓላማ ለአሁንም ይሁን ለቀጣዩ ትውልድ የሚበጅ ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን አንስቶ ለስኬቱ የሁላችንም ትብብር ያስፈልጋል ሲል ተናግሯል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች በአጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመምከር ለሀገር የሚበጅ መልካም ውጤት እንዲመጣ አደራቸውን እየተወጡ መሆኑ ይታወቃል።