ቀጥታ፡

ምክክሩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት አቅም ይፈጥራል- ነዋሪዎች

ቦንጋ ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት አቅም የሚፈጥር መሆኑን በቦንጋ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ለዘመናት ከቆዩ ችግሮቿን በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በምክክር የምትፈታበት ወርቃማ ጊዜ ላይ ትገኛለች።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለው አካታችና አሳታፊ የምክክር ጉባኤ የሀገሪቱን መፃኢ እድል የመወሰን አቅም ያለው ትልቅ መድረክ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቦንጋ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ለሰላም እጦትና ለእድገት ማነቆ ሆነው የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት አብነት ተመስገንና ወጣት ፈጠነ ወንድሙ እንደተናገሩት፥ ሀገራዊ ምክክሩ የውስጥ ችግርን በራስ አቅም መፍታት የሚያስችል ትልቅ እርምጃና የዘመናዊነት መገለጫ ነው።

ምክክሩ አካታች በሆነ መልኩ መካሔዱ ቅቡልነትን ያተረፈ ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በተለይም ወጣቶች በሀገራቸው ጉዳይ እንዲመክሩና እንዲወስኑ መደረጉ ለሀገር መፃኢ እድል ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት ወጣቶቹ ምክክሩ ለዘመናት ለሰላም እጦትና ለእድገት ማነቆ ሆነው የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ያስችላል ብለዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ተቹሬ ተክሌ በበኩላቸው፥ የምክክር ጉባኤዉ ኢትዮጵያን ከሚከሰቱ ግጭቶች በማላቀቅ ወደ ተሻለ ሰላምና ብልፅግና ያሸጋግራታል ሲሉ ተናግረዋል።

ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲመክሩና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ መደረጉ ትልቅ እምርታ መሆኑን ገልፀዋል።

አቶ ግርማ ገብረሚካኤል የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፥ የምክክር መድረኩ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ አለመግባባቶችንና ቅራኔዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ በምክክር በመፍታት ሰላምን የሚያፀና እና አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።

በግጭትና በጦርነት የተገነባ ሀገር የለም ያሉት አቶ ግርማ ምክክሩ፥ ኢትዮጵያዊያን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ የሚያሳይ ወርቃማ እድል ነው ብለዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ውይይት እየተደረገባቸው ያሉ ስምንት አጀንዳዎች ተገቢነት ያላቸውና የሀገርን የእድገትና የሰላም መፃኢ እድል የሚወስኑ በመሆናቸው ትልቅ ትስፋ እንዳላቸው አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም