ቀጥታ፡

በዞኑ ከ26ሺ ሔክታር  መሬት ላይ  የተሻሻሉ የቡና ችግኞች እየተተከሉ ነው

መቱ፣ሐምሌ 15/2018(ኢዜአ):- በኢሉባቦር ዞን በተያዘዉ ክረምት ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ ዝርያቸው የተሻሻሉና በአጭር ጊዜ   ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ እንደተናገሩት፤በዞኑ  በሽታን የሚቋቋሙ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡ እና ምርታማነታቸው የተረጋገጠ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በማቅረብ የተከላ ስራ እንዲጀመር ተደርጓል።

በዚሁ መሰረት በተያዘው የክረምት ወቅትም ከ26ሺ ሔክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ ከ200 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝን የመትከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚሁ ወቅት የቡና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንዲቻል  ልማቱን የማስፋትና የእንክብካቤ ስራዎችም እንዲጠናከሩ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአዲስ መሬትና በደረቁ የቡና ተክሎች ምትክ የቡና ችግኝ የመትከል ሥራ በሰፊው እየተከናወነ ሲሆን፣ ያረጁና ምርት የማይሰጡትን በመጎንደል  ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ የሁሩሙ ወረዳ አርሶ አደር ታምሩ ፈሪሳ ፤ከቡና ልማቱ በተሻለ መንገድ ተጠቃሚ ለመሆን በበጋው ወቅት የጎነደሏቸውን የቡና ተክሎች በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የቡና ልማቱን በማስፋት ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን እየተከሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

አርሶ አደር  ጌታቸው ጂፋርም በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ የቡና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ መሰማራታቸውን ነው የሚገልጹት።

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የተሻሻሉ የቡና ችግኝን በስፋት በመትከል ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ  እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢሉባቦር ዞን ከ72 ሺ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መሆናቸውን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት የተገኘው መረጃ  ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም