ቀጥታ፡

ምክክሩ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የታሪክ እና የልማት ምዕራፍ የምትሸጋገርበትን ዕድል የሚፈጥር ነው-ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ለዘመናት ስር ከሰደዱ ችግሮቿ ተላቃ ወደ አዲስ የታሪክ እና የልማት ምዕራፍ የምትሸጋገርበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እየተሳተፉ ያሉ ተመካካሪ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጰያዊያን ማህበረሰብ አባላት ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ምክክር የሚደረግባቸውን ስምንት አጀንዳዎች መለየቱ ይታወሳል።

በአጀንዳዎቹ ላይ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በተገኙበት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።

ከሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በንዑስ ቡድኖች በመከፋፈል በተመደቡበት አጀንዳ ላይ መመካከር ጀምረዋል።

በመካሄድ ላይ ባለው ጉባኤ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የዲያስፖራ ተወካይ ተመካካሪዎች ምክክሩ ኢትዮጵያ ከገጠሟት ዘመናት የተሻገሩ ችግሮች ወጥታ ወደ ተሻለ የታሪክ እና የልማት ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችላት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ የምክክር ሂደት ከታች ጀምሮ ችግሮቹን በምክክር እና በመግባባት እንዲፈታ መንገድ የከፈተ አዲስ ምዕራፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል ከአውስትራሊያ የመጡት ፓች አኩዌር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊት እንዲህ ባለው ሁኔታ ተመካክረው እንደማያውቁ ጠቁመው፤ ጥሪው በደስታ እና በሙሉ ስሜት የተቀበሉት መሆኑን ተናግረዋል።

ከሁሉም ክልሎች የመጡ ኢትዮጵያውያን የተሰበሰቡበት ድባብ እጅግ ደስ የሚል መሆኑን ጠቅሰው፤ ምክክሩ ለተተኪ ትውልድ የምትሆን ሀገር ለማስተላለፍ ትልቅ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ከአሜሪካ የመጡት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ጅምረናል ብለዋል።


 

የምክክር ሂደቱ የጋራ መግባባትን በመፍጠር ከግጭትና ከመነቃቀፍ ወጥቶ በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

አራት ሺህ ተመካካሪዎች ተሳትፎ የሚያደርጉቡት ይህ ምክክር ለኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል ብሩህ መሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

ይህ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካና ለዓለም ህዝብ ጭምር ትሩፋትና ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ታላቅ ሂደት ሲሉ ገልፀዋል።

ከእንግሊዝን የመጡት አለባቸው ደሳለኝ እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ ብሔረሰቦች እና ሲቪክ ማህበራት የተወጣጡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያሳዩት ቁርጠኝነትን አድንቀዋል።


 

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጰያዊያን ማህበረሰብ አባላት ለሀገር የሰላም ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በመመካከር የማይፈታ ችግር እንደሌለ ጠቁመው፥ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት ለማምጣት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም