ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የመሪነት ሚና እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የመሪነት ሚና እየተወጣች መሆኑን የናይጄሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አግቤዲ ፍሬደሪክ ገለጹ። 

ኢትዮጵያ አህጉራዊ ትብብርን በማጠናከር እና ልማትን በራስ አቅም ለማረጋገጥ የተጫወተችው ታሪካዊ ሚና እጅግ የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባል ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በፓርላማ ሥርዓት ረጅም ታሪክ ካላቸው ሀገራት አንዷ እንደመሆኗ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እያበረከተች ያለው ሚና የሚደነቅ ነው። 

በተለይም አህጉራዊ ትብብርን እና በራስ አቅም የመቆም አቅጣጫን ለማጎልበት የተጫወተችው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል። 

ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ማጠናቀቋም ለዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየችበት መሆኑን ተናግረዋል። 

ለዴሞክራሲ ሥርዓት  ግንባታ በዋነኝነት የሚያስፈልገው የዜጎችን ፍላጎት የሚመልስ፣ ሰላምን የሚያሰፍንና ሀገራዊ እድገትን የሚያፋጥን ኃላፊነት የሚሰማው አመራር መሆኑንም አስገንዝበዋል። 

በመሆኑም ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የምታደርገው ተጨባጭ ጥረት እና እያስመዘገበችው ያለው ስኬት ለአፍሪካ ብርሃን ፈንጣቂ አድርጓታል ብለዋል።

የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ያነሱት የምክር ቤት አባሉ በሀገራቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች መካከል የተመሰረተው የፓርላማ ወዳጅነትና የፓርላማ ግንኙነትን ለማጠናከር የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም የሀገራቱን የዲሞክራሲ ተቋማት የማጠናከር ተግባር ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ትብብርና ሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ትብብርና በራስ አቅም መቆም በማጎልበት ረገድ የተጫወተችውን ታሪካዊ ሚና አድንቀዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በእርስ አጋርነትና ትብብርን ለማጠናከር  በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም