ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤውን ሀገራት ስትራቴጂክ የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2018( ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤውን ሀገራት ስትራቴጂክ የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ገለጹ።

የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤው (ገልፍ) ሀገራትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር የባሕረ ሰላጤውና አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

በመድረኩ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት በአፍሪካ የሚኖራቸውን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ በማስፋፋት በስትራቴጂክ አጋርነት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ የኢኮኖሚ ሽግግርን ማፋጠን የሚያስችሉ ጉዳዮች ይመከርባቸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የብዝኅ ዘርፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብርም የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የልማት ምኅዳርን ፈጥሯል።

መድረኩም የባሕረ ሰላጤው ሀገራት በኢትዮጵያ ያላቸውን ዘመናትን የተሻገረ ስትራቴጂክ አጋርነት በሁሉም የልማት መስክ የበለጠ ለማሳደግ ወሳኝ አጋጣሚ መሆኑ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በዚሁ ወቅት፤ የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ስትራቴጂክና ዘላቂ አጋርነት የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ሽግግር ምዕራፍም በዓለም ላይ በፍጥነት ከሚያድጉ አሥራ አምስት ኢኮኖሚዎች መካከል ሰባቱ በአህጉሪቱ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ብለዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትም ግዙፍ የዓለም አቀፍ የንግድ ቀጣና በመፍጠር ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት አዳዲስ ዕድሎችን እየከፈተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም አፍሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን በማስፋት የምግብ ዋስትና፣ ታዳሽ ኃይልና ለዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ስትራቴጂካዊ አጋር እየሆነች መምጣቷን ተናግረዋል።

የባሕረ ሰላጤው ሀገራትም የሉዓላዊ ሀብት ፈንዶችን በመጠቀም በመሠረተ ልማት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስና በግብርና ዘርፎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል።

በቀጣይ ትብብርን በማጠናከር አስተማማኝና ሳቢ የኢንቨስትመንት ሕግና ፖሊሲ ማዕቀፍ በመፍጠር ፈጠራ የታከለበት ጠንካራ የትግበራና የክትትል ስልት ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትና የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ የአህጉሪቷንና የባሕረ ሰላጤው ሀገራትን ስትራቴጂክ አጋርነት በማጠናከር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሽመልስ ኃይሉ በበኩላቸው፤ የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ስትራቴጂክ አጋርነት ለኢኮኖሚ ሽግግርና ዘላቂ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ኢንቨስትመንት በመሠረተ ልማት፣ በሎጂስቲክስ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በፋይናንስና በዲጂታል ፈጠራዎች ላይ እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር አፍሪካን ከዓለም አቀፍ ገበያዎች ጋር የሚያገናኝ ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሮች መተግበራቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም