የአፍሪካ ሕብረት የጤና ዘርፍ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በጋና አክራ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሕብረት የጤና ዘርፍ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በጋና አክራ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የበርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የሚታደሙበት የአፍሪካ ሕብረት የጤና ዘርፍ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በጋና ይካሄዳል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአፍሪካ ሕብረት ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ትናንት የጋና መዲና አክራ መግባታቸው ይታወቃል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩዜቶ አብላክዋ እና ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ስኬታማ ተሞክሮዎችና ለአህጉራዊ ግቦች ያላትን ተጨባጭ ቁርጠኝነት ለጉባኤው እንደሚያጋሩ ይጠበቃል።
በጤና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ይህ ልዩ አህጉራዊ ጉባኤ የተዘጋጀው፣ በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ሲሆን፣ ዓላማውም በአፍሪካ እየተለዋወጡ ባሉ የጤና ቀዳሚ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ማዘጋጀት ነው።
ጉባኤው ቀደም ሲል የተወሰኑ ውሳኔዎችን እና አህጉራዊ ቃል ኪዳኖችን መሠረት በማድረግ፣ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል ሥራን አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ የማይበገር የጤና ሥርዓትን ለመገንባት እና በአህጉሪቱ የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሙሉ በሙሉ ወጪው የተሰላለት የአፍሪካ ህብረት የ2030 እና ከዚያ በላይ ፍኖተ ካርታ ላይ ይመክራል።
ጉባኤው "ፍትሕን፣ እኩልነትን እና ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ማሳደግ፤ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን እና ቲቢን ማስወገድ፣ የእናቶችን ጤና ማሻሻል፣ በአፍሪካ ተላላፊ ያልሆኑ እንዲሁም ችላ ለተባሉ የሐሩራማ በሽታዎች መፍትሔ መስጠት" በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።
ጉባኤው ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነትን ለማንቀሳቀስ፣ ስትራቴጂካዊ ትግበራዎችን ለማጠናከር፣ ዘላቂ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጭን ለመጨመር፣ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ማምረትን ለማስፋፋት እና በአጀንዳ 2063 የምንመኛትን አፍሪካ ራዕይን ለማሳካት የአፍሪካን የጤና ቀዳሚ ጉዳዮች ትግበራ ለማፋጠን ያለመ ነው።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከተደረጉ ዘላቂ ኢንቨስትመንቶች የተነሳ እ.ኤ.አ. ከ2004 ጀምሮ ከኤድስ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሞት በ74 በመቶ ቀንሷል። በሌሎችም የጤና ጉዳዮች እንዲሁ ለውጦች መጥተዋል።
ሆኖም እየቀነሰ እና ግምት የማይሰጠው እየሆነ የመጣው የውጭ ፋይናንስ እነዚህን ስኬቶች ስጋት ላይ እየጣላቸው መሆኑ፣ በአፍሪካውያን የገንዘብ፣ የተቋምና ውሳኔ ሰጪነት የሚመሩ እና የሚደገፉ የጤና ሥርዓቶችን ማጠናከር አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑን ያሳያል።
አባል ሀገራት ከሀገራዊ በጀታቸው ቢያንስ 15 በመቶ ለጤና ዘርፍ እንዲመድቡ ከሚጠይቀው የአቡጃ ቃል ኪዳን ጋር በተጣጣመ መልኩ፣ ጉባኤው የ2030 እና ከዚያ በላይ አህጉራዊ ፍኖተ ካርታን በፍጥነት ለመተግበርና ለማሳካት የሀገር ውስጥ ጤና ፋይናንስን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን ይመረምራል።
እንዲሁም በቲቢ፣ በወባ፣ በእናቶች እና በጨቅላ ሕፃናት ጤና፣ በሄፓታይተስ ቫይረስ፣ ችላ በተባሉ የሐሩራማ በሽታዎች እና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ይመክራል።