ቀጥታ፡

የእንጦጦ-ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት ለዜጎች ስብዕና ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ፕሮጀክት ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የእንጦጦ-ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት የአካባቢውን ጉስቁልና በመቀየር ለዜጎች ስብዕና ግንባታና የአዕምሮ እረፍት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ፕሮጀክት መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእንጦጦ-ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት እንዲሁም የቀበና ግድብን ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም መርቀው ክፍት ማድረጋቸው ይታወቃል።


 

በዚሁ ወቅትም፤ ፕሮጀክቱ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ በማድረግ ተጨማሪ ውበትና ገፅታ በማላበስ ከተማዋን የዓለም አቀፍ ቱሪዝምና የኢኮኖሚ ማዕከል የማድረግ ስልታዊ ሽግግር አካል መሆኑን ገልጸዋል።

የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቱ የወንዝ መከላከያ ግንቦች፣ ዘመናዊ ድልድዮችና ሰፊ አረንጓዴ ሥፍራዎችን በማካተት 87 ነጥብ 6 ሔክታር መሬትና 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይሸፍናል።

የመዲናዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የእንጦጦ-ቀበና ፕሮጀክት ያረፈበት ሥፍራ ከዚህ ቀደም በንጽህና ጉድለት በእጅጉ የተጎሳቆለና ለጤና ጠንቅ የነበረ አካባቢ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት መገንባቱ የነዋሪዎችን አካላዊና አዕምሯዊ መንፈስ በማደስ ከከተማው ተፈጥሮ ጋር በተሰናሰለ መልኩ ማራኪና አረንጓዴ መዝናኛነት መቀየሩን ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ሲሳይ እንዳለ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል አካባቢው ለደህንነት እጅግ አሳሳቢ እና ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት ሕብረተሰቡ በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ የሚገድብ ነበረ።

አሁንም የከተማዋን ገጽታ በሚመጥንና ደረጃውን በሚጠብቅ መልኩ ተገንብቶ ለአገልግሎት መዘጋጀቱ ለልጆችና ለነዋሪዎች አካላዊና አዕምሯዊ ዕድገት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ሳሙኤል ሰለሞን በበኩሉ፤ የእንጦጦ-ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የተከናወኑት ማራኪ የልማት ሥራዎች ከተፈጥሮ ጋር በእጅጉ ቁርኝትን ፈጥረዋል ብሏል።

የእንጦጦ-ቀበና የልማት ፕሮጀክት የቱሪዝም ገቢን በማሳደግ ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀትና ለነዋሪዎች ምቹ የከተሜነት እንቅስቃሴ ምኅዳርን የፈጠረ ነው ያሉት ደግሞ አንተነህ እሸቱ ናቸው።


 

ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ ወጣት ቤተልሔም ታደሰ እንዳለችው፤ አዲስ አበባን ጨምሮ የኢትዮጵያ የልማት ውጤታማ ጉዞ ገፅታን በመገንባት ወጣቶች የልማት አካል የሚሆኑበትን ከፍተኛ ተነሳሽነት የፈጠሩ ናቸው።


 

ለዘመናት ቀጥሎ የቆየው የቀበና እና አካባቢው ቆስቋላ ገፅታ በነዋሪዎች እንቅስቃሴና ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትል ነበር ያሉት ደግሞ ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ አቶ ታምራት ቀለቤቶ ናቸው።


 

አሁን ላይ በእንጦጦ-ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ማራኪ ገፅታን በመላበስ ለመዲናዋ ነዋሪዎች ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም