የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአፍጥር የተፈጥሮ ደን ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአፍጥር የተፈጥሮ ደን ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር እያስቻለ ነው
ወልቂጤ ፤ ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአፍጥር የተፈጥሮ ደን ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር እያስቻለ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የአፍጥር የተፈጥሮ ደን በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ከሚገኙ የተፈጥሮ ደኖች ከቀዳሚዎች መካከል ይጠቀሳል።
ደኑን በመጠበቅ ብዝሃ-ህይወትን ለማቆየትና የአየር ጸባይ ለውጥን ለመከላከል እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚኖረውን ኢኮኖሚና ማህበራዊ ፋይዳ ለማጉላት እየተሰራ ነው።
ተግባሩን ለማስቀጠልም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ትልቅ አጋዥ ሆኖ እያገለገለ መሆኑም ተጠቅሷል።
የቸሃ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጠቅልል አባድየ እንዳሉት 40 ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የአፍጥር ደን ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆን ጥበቃ እየተደረገለት ነው።
ደኑ የአካባቢውን የስነ-ምህዳር ሚዛን እንዲጠበቅና ወጣቶች በደኑ በንብ ማነብ እንዲሁም በመኖ ሳር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ደኑ ለአፍጥር ከተማም ውበትና የመስህብ ስፍራ በመሆን እያገለገለ መሆኑን አመልክተዋል።
የደን ጥበቃው የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል ባለፈ ለከርሰ-ምድር ውሃ ምንጭነት ያለውን አቅም ለማስቀጠል በክፍት ቦታዎች ላይ ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ስራ መከናወ ኑን ጠቅሰዋል።
ህዝቡ ለደኑ ጥበቃና እንክብካቤ ከማድረግ ባለፈ ሳሳ ባሉ የደኑ ክፍሎች የሀገር በቀል ዛፎች እየተከለ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በአፍጥር ደን ዙሪያ ከሚገኙ ነዋሪዎች መካከል አቶ ደንጭዛ ጃጃተ ናቸው።
እንደ ዝግባ፣ ጽድ፣ ዋንዛና ሌሎች የሀገር በቀል ዛፎች ጥበቃ የማድረግ ማህበረሰባዊ እሴትም ለስራው ውጤታማነት ማገዙን ተናግረዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ደንን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ባህልን ከአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ጋር በማጣመር እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ፍቃዱ አመርቻ ናቸው።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ደኑን በመንከባከብና በክፍት ቦታዎች ላይ ሃገር በቀል ችግኝ በመትከል ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ዘጠኝ ሆነው በመደራጀት የሃገር በቀል ዛፎች ችግኝ በማፍላትና በማዘጋጀት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እያቀረቡ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት ያለው ተረጋ ነው።
በአካባቢው ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የገበያ እድል እንደፈጠረላቸውና የአፍጥር ደንም ለሚያዘጋጇቸው ችግኞች የዘር ምንጭ መሆኑን አመልክቷል።