የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል በስኬት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል -ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል በስኬት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል -ፖሊስ
ሀረር ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊው የንግስ በዓል በስኬት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
በአመታዊ የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚመጡ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተጨማሪ ቱሪስቶች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች እንግዶች ይታደማሉ።
የንግስ በዓሉም በሰላምና በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊና የአካባቢው ጊዜያዊ የጸጥታ ግብረ ሃይል ሰብሳቢ ረዳት ኮሚሽነር ናስር መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበዓሉ ወቅት ወንጀል እንዳይፈጸም የህግ አስከባሪዎች የተቀናጀ ስራ ለማከናወን ተሰናድተዋል።
ለበዓሉ ሰላማዊነትም የተለያዩ የጸጥታ አካላት ከወዲሁ ተዘጋጅተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎችም ወደ በዓሉ ስፍራ ሲጓዙ ንብረቶቻቸውን በጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በአካባቢው ዳገት፣ ቁልቁለት እና ጠመዝማዛ መንገድ ስለሚበዛና ወቅቱም ክረምት ስለሆነ አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ ባለፈ የትራፊክ ህግና ደንብ አክብረው እንዲያሽከረክሩም ረዳት ኮሚሽነር ናስር አስገንዝበዋል።