ቀጥታ፡

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን አጠናክሮ በማስቀጠል ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጎልበት ይገባል

ደብረ ብርሃን፤ ሐምሌ 14/ 2018(ኢዜአ)፡- ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን አጠናክሮ በማስቀጠል ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚገባ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ገለጹ።

"በጎነት ለኢትዮጵያ  ከፍታ" ቁጥር-5 አገር አቀፍ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በደብረ ብርሃን ከተማ በጫጫ ክፍለ ከተማ ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ በድሉ ውብሸት በአቀባበሉ ላይ እንደገለጹት ከለውጡ ወዲህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ባህል እየሆነ መጥቷል።


 

በዚህም ወጣቶች በአካባቢያቸው ከሚያከናወኑት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ባሻገር ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ መሰማራታቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ይህም ወንድምና እህትማማችነትን በማጎልበት በኢትዮጵያ  ህብረ ብሄራዊ አንድነት ከማጠናከር አንፃር እየተከናወኑ ያሉ  ተግባራትን ይበልጥ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በወሰን ተሻጋሪ አገልግሎት የሚሳተፉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም በሚሄዱባቸው አካባቢዎች የህብረተሰቡን ባህል፣ ወግና እሴት በመገንዘብ የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጠናከር እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የቱሪስት መዳረሻቸውን እንዲጎበኙና እንዲያውቋቸው ለማድረግም ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።


 

በአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም አረጋ በበኩላቸው፤  ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን  በማጠናከር አገራዊ አንድነትን ለማጎለብት የሚያስችል ነው።

ወጣቶች እርስ በእርስ በመተዋወቅ አብሮ በመስራት ለመጪው ትውልድ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ እንደሚያስችላቸውም ነው ያስገነዘቡት።

የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የቡድን አስተባባሪ አቶ እንደገና ፍቃዱ በበኩሉ ፤ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት አፋርና ሱማሌን ጨምሮ ዛሬ አምስተኛ መዳረሻቸውን ደብረ ብርሃን ማድረጉን ነው የተናገረው።


 

ቡድኑ በአረጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ በደም ልገሳ፣ አረጋዊያንን በመንከባከብና በሌሎች የልማት ስራዎች እንደሚሳተፍም አስረድቷል።

በደብረ ብርሃን ከተማ በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ጠቁመው በሚኖራቸው ቆይታ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚሰሩም ነው ያረጋገጠው።

በአዲስ አበባ መስተዳድር ወጣቶች ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ፍራኦል ደበላ በበኩሏ ፤የበጎ ፈቃድ ስራው በተለይ ወጣቶች በሚሰማሩበት አካባቢ አዳዲስ የህይወት ክህሎት፣ ልምዶችና ባህሎችን አንዲጋሩ ለማድረግ ያስችላል ብላለች።


 

ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከ40 በላይ ወጣቶች በደብረ ብርሃን ከተማ በመገኘት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ባሻገር ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።

በአማራ ክልል በተያዘው ክረምት 15ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች  ተግባራዊ እንደሚደረጉ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም