አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የሶስት ሚሊዮን ዶላር የአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ለለውጥ አሸናፊ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የሶስት ሚሊዮን ዶላር የአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ለለውጥ አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ለለውጥ (AHEFT) የመጀመሪያው ዙር ሽልማት አሸናፊ በመሆን ተመርጧል።
ዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ለውጥን በመምራት እና ለወጣቶች ዕድሎችን በማስፋፋት ዕውቅና ከተሰጣቸው አምስት የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል።
ሽልማቱ በምርምር፣ በፈጠራ፣ በሰው ኃይል ልማት እና በማህበረሰብ ተፅዕኖ ላይ የሚደረገውን ሥራ የበለጠ ለማጠናከር የሚረዳ የ3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍን ያካተተ ነው።
ይህ ዕውቅና "Reimagining Our Future" የተሰኘውን ስትራቴጂክ ዕቅድ እና ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት የሚያንፀባርቅ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
እንደ ኢትዮጵያ አንጋፋ፣ ስመ-ጥር እና ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ፣ ይህንን ዕድል ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ የሚሆን የምርምር ብቃት፣ ፈጠራ እና ለውጥ አምጪ ትምህርትን ለማጠናከር እንደሚጠቀምበት ገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው ለዚህ ዕውቅና ማስተርካርድ ፋውንዴሽንን አመስግኖ፣ ለዚህ ስኬት አስተዋፅኦ ላደረጉ መምህራን፣ ሰራተኞች፣ የነበሩና የአሁኑ ተማሪዎች እንዲሁም አጋሮች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።