በመግባባት መንፈስ እየመከርን ነው - የዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በመግባባት መንፈስ እየመከርን ነው - የዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ)፦ በመግባባት መንፈስ እየመከሩ እንደሚገኝ የዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች አስታወቁ።
ምክክሩ የዘመናት ጥያቄዎችን መልስ እንደሚያስገኝ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ምክክር የሚደረግባቸውን ስምንት አጀንዳዎች መለየቱ ይታወሳል።
በአጀንዳዎቹ ላይ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በተገኙበት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።
ከተመካካሪዎቹ መካከል አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ምክክሩ አካታች በሆነ መንገድ ተመካካሪዎቹን መምረጡን በአካል በመሳተፍ አረጋግጠዋል።
በምክክሩም ሕዝብ የተሳተፈበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የምክክሩ ሌላው ጠንካራ ጎን መሆኑን አመልክተዋል።
ምክክሩ በኢትዮጵያውያን ተወጥኖ በራሳቸው መፍትሔ የሚበጅለት መሆኑ ከሌሎች ሀገራት ልዩ ያደርገዋል ያሉት አቶ ቀጄላ፤ የኢትዮጵያ የምክክር ሂደት ለሌሎች ሀገራትም አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል።
አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ምክክር እንዲደረግ ሊቃውንት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ዜጎች ለዘመናት ሲጠይቁት የነበረ ጉዳይ መሆኑን አስታውሰዋል።
አሁን የጀመርነው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለዚያ ጥያቄ መልስ የሰጠ ነው ያሉት አርክቴክት ዮሐንስ፤ ሁሉም በጋራ ሆኖ ልዩነቱን ተመካክሮ መፍትሔ የሚያበጅበት ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል ብለዋል።
ምክክሩ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደፊት ልዩነቶችን ለመፍታት ኃይል ሳይሆን የሰለጠነ አካሄድ እንዲሆን መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ ወጣት አርአያም ጽጌ በሰጠው አስተያየት፤ ምክክር የጋራ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጿል።
ምክክሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ምቹ መድረክ የሚፈጠርበት መሆኑን ጠቅሶ፤ ሂደቱ በመከባበር፣ በመተባበርና በመግባባት መንፈስ እየተሳተፍንበት ነው ብሏል።
ሌላው የምክክሩ ተሳታፊ ቶፊቅ ሀጫሉ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ምክክር ባለመደረጉ በመግባባት የሚፈቱ ጉዳዮች ዋጋ ማስከፈላቸውን ገልጸዋል።
መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ምክክሩ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ገልጸው፤ በምክክሩ ላይም አሳታፊና ያለገደብ ሐሳብ እየሰጠን ነው ብለዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ ባንዲራ በላቸው በበኩላቸው፤ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔዎችን ማመላከት የሚያስችሉ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈልቁ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተመልክቻለሁ ብለዋል።