በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሂደት መግባባትን የሚፈጥር ግልፅና ተስፋ ሰጪ ምክክር እያደረግን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሂደት መግባባትን የሚፈጥር ግልፅና ተስፋ ሰጪ ምክክር እያደረግን ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሂደት ጠንካራ መግባባትን የሚፈጥር ግልፅና ተስፋ ሰጪ ምክክር እያደረግን ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመካካሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዋናው የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።
በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች ሕዝብ የወከላቸው ተመካካሪዎችም ከትናንት ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በንዑስ ቡድኖች በመከፋፈል በተመደቡበት አጀንዳ ላይ መመካከር ጀምረዋል።
የምክክሩ ሂደት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈና በግልጽነት መርህ ላይ በተመሠረተ መልኩ እየተካሄደ ሲሆን፤ ለብዝኃነት ዕውቅና በመስጠት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በእያንዳንዱ ንዑስ ቡድን ውስጥ 50 ተመካካሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 80 አነስተኛ ቡድኖች በተመደቡላቸው አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።
በአንድ አጀንዳ ላይ እንዲመክር 500 ተመካካሪዎችን በሥሩ የያዘ ዐቢይ ቡድን፣ እያንዳንዳቸው 50 ተመካካሪዎችን የያዙ 10 የሚሆኑ ንዑስ ቡድኖችን በመያዝ ተዋቅሯል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ከመላው ሀገሪቷ የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ኮሚሽኑ ለምክክሩ በመረጣቸው ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያ በመመካከር ላይ ናቸው።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች እንዳሉትም፤ በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ግልጽና ተስፋ ሰጪ ሂደት ላይ ምክክር እያደረጉ ነው።
የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ጉባኤ የመደማመጥና የጋራ መግባባት ባህልን በማጠናከር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
ከተመካካሪዎች መካከል ሲሳይ ዘለቀ፤ የምክክር መድረኩ የሀገሪቱን የጋራ የወደፊት ዕድል ለመወሰን ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ገልጸዋል።
ሁሉም ተመካካሪዎች ለሀገር ይበጃል ያለውን ሐሳብ በማዋጣት በግልጽነት እየተመካከረ እንደሚገኝ ተናግረው፤ እስካሁን ያለው ሂደት ፍጹም ግልጽና ተስፋ በተሞላበት መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ መምህር ሞገስ ፍሥሓ በበኩላቸው፤ በመጀመሪያ ደረጃ የምክክር መድረኩ እርስ በእርስ እንድንተዋወቅ ዕድል ፈጥሮልናል ብለዋል።
ሂደቱ በጣም ደስ በሚል ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ መድረኩ ተመካክረንና ተወያይተን አዲሷን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክክር አንዱ የሌላውን ሐሳብ በማዳመጥ መግባባት መፍጠር ነው ያሉት ሌላኛው ተመካካሪ ናስር አብደላ፤ በምክክር ጉባኤውም ሁሉም ተመካካሪ ሐሳቡን በነፃነት እየገለጸና እየመከረ ነው ብለዋል።
የምክክሩን አሁናዊ ሂደት በማድነቅ፣ ሂደቱ ከመከራከር ይልቅ የመደማመጥና የመመካከር ባህልን የሚከተል መሆኑን ገልጸዋል።