ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለማጽናትና ጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በሚያስችሉ አጀንዳዎች ላይ ምክክር እያደረግን እንገኛለን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለማጽናትና ጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በሚያስችሉ አጀንዳዎች ላይ ምክክር እያደረግን እንገኛለን
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለማጽናትና ጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በሚያስችሉ አጀንዳዎች በሠለጠነ መንገድ ምክክር እያደረግን እንገኛለን ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች ከትናንት ጀምሮ በንዑስ ቡድኖች በመከፋፈል በተመደቡበት አጀንዳ ላይ መመካከር ጀምረዋል፡፡
የምክክሩ ሂደት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈና በግልጽነት መርህ ላይ በተመሠረተ መልኩ እየተካሄደ ሲሆን፤ ለብዝሃነት ዕውቅና በመስጠት በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በእያንዳንዱ ንዑስ ቡድን ውስጥ 50 ተመካካሪዎች ሲገኙ፤ በአጠቃላይ 80 አነስተኛ ቡድኖች በተመደቡላቸው አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ናቸው።
በአንድ አጀንዳ ላይ እንዲመክር 500 ተመካካሪዎችን በሥሩ የያዘ ዐቢይ ቡድን፣ እያንዳንዳቸው 50 ተመካካሪዎችን የያዙ 10 የሚሆኑ ንዑስ ቡድኖችን በመያዝ ተዋቅሯል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ኮሚሽኑ ለምክክሩ በመረጣቸው ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያ በመመካከር ላይ ናቸው።
የምክክር ጉባኤው ተመካካሪ ሻምበል አለማየሁ ታፈሰ እንደገለጹት፤ በአንድ ሀገር የሚገኙ ዜጎች በማያግባቡ ጉዳዮች ላይ በምክክር የጋራ መግባባት መፍጠር ለሀገራዊ አንድነት ፋየዳው የላቀ ነው።
ለዚህም እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ስር በሰደዱ ጉዳዮች ዙሪያ በሰከነና በሰለጠነ መንገድ በመመካከር ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እየመከርን ነው ብለዋል።
የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያነሱትን ሐሳብ በማዳመጥና የራሳቸውን ሐሳብ በማካፈል ለሀገር ይበጃል የሚል ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ በሰለጠነ መንገድ እየተመካከሩ መሆናቸውን አክለዋል።
ተመካካሪ ዝማማ አቡሃይ በበኩላቸው፤ በምክክሩ ሀገርን የሚያሻግር መፍትሔ እንድናመጣ ሀገርና ሕዝብ አደራ ጥሎብናል ብለዋል።
ተመካካሪዎችም ይህንን ታሪካዊ አደራ በብቃት ለመወጣት ሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የምክክሩ ሂደት ሁሉንም ያካተተ መሆኑ የተለያዩ ዕይታዎችና ሃሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ እንዲሁም የኢትዮጵያን ብዝሃነት የጠበቀ ውይይት እንዲደረግ ትልቅ አቅም ፈጥሯል ሲሉ ገልጸዋል።
ተመካካሪ ሊዲያ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ በምንመካከርባቸው አጀንዳዎች ላይ ሐሳባችንን በነፃነት በማቅረብ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለን ያሰብነውን መፍትሔ ለማምጣት እየተጋን ነው ብለዋል፡፡
በምክክሩ ሂደት ባለቸው ተሳትፎም የራሳቸውን ሐሳብ ከማካፈል ባለፈ፣ ከሌሎች ተመካካሪዎች የሚነሱ ሃሳቦችን በመስማት ጥሩ የምክክር ጊዜ እያሳለፉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በጉባኤው ላይ ከተለያዩ አጀንዳዎች መመካከር ባለፈ ከተለያየ አካባቢ የመጡ ዜጎች እርስ በእርስ በደንብ እንዲተዋወቁ እንዳገዛቸው ገልጸዋል።
አራት ሺህ ተመካካሪዎች እየተሳተፉበት የሚገኘው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።