ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአፍሪካ ሕብረት የጤና ዘርፍ ጉባኤ ለመሳተፍ ጋና ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአፍሪካ ሕብረት የጤና ዘርፍ ጉባኤ ለመሳተፍ ጋና ገቡ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአፍሪካ ሕብረት የጤና ዘርፍ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ጋና ገብተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ኦኩዜቶ አብላክዋ እና ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ልዩ ጉባኤ በጤና ዘርፍ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዋናነትም እ.ኤ.አ. በ2030 በአህጉሪቱ ኤች አይ ቪ ኤድስን ከሕብረተሰብ ጤና ስጋትነቱ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ፣ የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞትን መግታት፣ በአህጉሪቱ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር፣ እንዲሁም የጤና ስርዓቶችን በስትራቴጂካዊ ባለቤትነትና በራስ አቅም ለማጠናከር የሚያስችል ዘላቂ የፋይናንስ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ላይ ይመክራል።
በጉባኤው የኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ስኬታማ ተግባራትን ተሞክሮ ለአህጉሪቱ መሪዎች ታካፍላለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋና በሚኖራቸው ቆይታ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን ይበልጥ በሚያጠናክሩና ቀጣናዊ ትብብርን በሚያሳድጉ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ውይይቶችን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።