ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመመከት ረገድ የማይተካ ሚናዋን እየተወጣች ነው-አምባሳደር ሃደራ አበራ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ ገለጹ።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት 1354ኛ የሚኒስትሮች ስብሰባውን ዛሬ በበይነ መረብ አካሂዷል።


 

ስብሰባው በአፍሪካ ሽብርተኝነትና በዓመፅ የታጀበ ጽንፈኝነትን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ በስብሰባው ላይ ተሳትፈዋል።

አምባሳደር ሃደራ አበራ ዓለም አቀፍ የሽብርተኛ ቡድኖች በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት የደቀኑትን ስጋት አንስተዋል።

የሽብርተኛ ቡድኖች ዲጂታል አማራጮች እና ማህበራዊ ሚዲያ ጨምሮ ቴክኖሎጂዎችን አባላትን ለመመልመል፣ ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት እና ጽንፈኝነትን ለማስፋፋት እየተጠቀሙበት እንደሚገኝ አመልክተዋል።


 

ዓለም ላይ ያሉ ለውጦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይልን ወደ ስራ ማስገባት እና የአፍሪካ ሀገራት በደህንነት እና አስተዳደር ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ አህጉራዊ የአሰራር ማዕቀፎችን በሚገባ መተግበር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አምባሳደር ሃደራ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ሽብርተኝነትን ለመከላከል እና በቀጣናው ያለውን የሽብርተኝነት ነቀርሳ ለማስወገድ እያደረገች ያለውን የማይተካከል አስተዋጽኦ ማንሳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም