ኢትዮጵያ እየመከረች ነው! - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!
የሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ዐበይት መረጃዎች
በትናንትናው ዕለት በቡድን ተከፋፍለው መመካከር የጀመሩት ተመካካሪዎች ዛሬም በየቡድናቸው በመሆን መመካከር ቀጥለዋል፡፡
50 ተመካካሪዎችን በመያዝ በ80 ቡድን ተከፋፍለው መመካከር የጀመሩት ንዑሳን ቡድኖች በተሟላ ሁኔታ ከትላንት ከሰዓት ጀምሮ በየንዑስ ቡድናቸው አስር አስር በመሆን ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሂደት እስከ ነገ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በዚህ ሂደት ተመካካሪዎች በሚመካከሩባቸው የአጀንዳ ሃሳቦች ላይ በርካታ ሃሳቦችን እና ምልከታዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ሂደቱ ተመካካሪዎች ላለመግባባት መንስኤ የሆኑ እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ አመለካከቶችን እና ምክንያቶችን ከስር መሰረቱ አንዳቸው ሌላቸውን እንዲረዱ መደላድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡
ይህንን ሂደት ለማሳካት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ ተቋማት በሙያቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው እና ለአጀንዳ ሃሳቦቹ ባላቸው ሙያዊ ቅርበት ብቁ ናቸው ብሎ ያመነባቸው 80 የሚጠጉ የባለሙያዎች ስብስብ (Panel of Experts) በማሰባሰብ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ እያሳተፈ ይገኛል፡፡
የባለሙያዎች ስብስብ በአጀንዳ ነጥቦች ላይ ለሚፈጠሩ ብዥታዎች ማብራሪያ በመስጠት ሂደቱን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል በዚህ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተለያዩ የሀገር ውስጥ ተቋማት ሂደቱን ለመታዘብ ለኮሚሽኑ ጥያቄ ባቀረቡት መሰረት ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት፣ ከተለያዩ የሙያ ማህበራት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ እና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተውጣጡ ከ50 በላይ ገለልተኛ ታዛቢዎች የምክክር ሂደቱን እየታዘቡ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም