ለባሌ ሮቤ አጠቃላይ ሆስፒታል እና አጋርፋ ጤና ጣቢያ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለባሌ ሮቤ አጠቃላይ ሆስፒታል እና አጋርፋ ጤና ጣቢያ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
ሮቤ፣ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የባሌ ሮቤ አጠቃላይ ሆስፒታልና አጋርፋ ጤና ጣቢያ 200 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገላቸው።
ድጋፉን ያደረጉት 'ፕሮጄክት ኪዩር' እና 'ኢስላሚክ ሪሊፍ' የተባሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሆናቸው ተገልጿል።
የቁሳቁሶቹን የትራንስፖርት ወጪ በመሸፈን የሶፍ ዑመር የሚኒሶታ ማኅበረሰብ ማኅበር እና መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ድርሻቸውን መወጣታቸው ተገልጿል።
በርክክቡ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ኢሳ ሀሰን (ረዳት ፕሮፌሰር) እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ችግር ለመፍታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ነው።
በተለይ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ተግባር በተጓዳኝ በምርምርና ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው በሚገኙ የጤና ተቋማት የሕክምና ቁሳቁሶችን ተደራሽ በማድረግ አገልግሎቱን ለማሻሻል የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሕክምና ቁሳቁሱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ውክልናን በመውሰድ፣ የጉምሩክ፣ የግብር እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎችን በመሸፈን ለተጠቃሚው እንዲደርሱ መደረጉን ገልጸዋል።
ድጋፉ በሆስፒታሉ የሚታየውን የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት በማቃለል ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት ይበልጥ ለማሻሻል ያግዛል ያሉት ደግሞ የባሌ ሮቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ኃይሉ ናቸው።
በድጋፍ ከተገኙ የሕክምና መሣሪያዎች መካከል የሕሙማን አልጋ፣ በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚያገለግሉ መሣሪያዎች፣ ማሞቂያ (ኢንኩቤተር)፣ አልትራ ሳውንድ እና ሕሙማን ማመላለሻ የአካል መደገፊያዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
የሕክምና ቁሳቁሱን ድጋፍ ውጤታማነት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ የተቋማት ተወካዮች የዕውቅናና ባህላዊ አልባሳት ተበርክቶላቸዋል።