ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ህብረተሰቡ በአቅራቢያው የተቀላጠፈ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ እያስቻሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ህብረተሰቡ በአቅራቢያው የተቀላጠፈ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ እያስቻሉ ነው
ሚዛን አማን፣ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ)፦ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ህብረተሰቡ በአቅራቢያው የተቀላጠፈ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ እያስቻሉ መሆኑን የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ቤተልሔም ዳንኤል ለኢዜአ እንዳሉት፥ በ2016 ዓ.ም ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን በክልሉ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል።
በዚህም የማህበረሰብ ፍትሕ ላይ በማተኮር 758 ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን አደራጅቶ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ ከ2 ሺህ 400 በላይ መዝገቦች መታየታቸውን አስታውቀዋል።
ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ ለህብረተሰቡ በአቅራቢያ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት በመስጠት የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብን ብክነትን ማስቀረታቸውን ተናግረዋል።
በተያዘው አዲስ የበጀት ዓመት ተግባሩን በሁሉም የክልሉ ቀበሌዎች በማስፋፋት ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን መጠን 960 ለማድረስ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በክልሉ ሞዴል ከሆኑ የቀበሌ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች መካከል በካፋ ዞን ሺሺንዶ ከተማ አስተዳደር የአበች ቀጠና 2 ባህላዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ መምህር ከበደ ወልደሚካኤል በሕዝቡ በባህላዊው ስርዓት መሰረት ፍርድ እንዲያገኝ እየሰራን ነው ብለዋል።
አባቶቻችን ያወረሱንን ሰላም መጠበቂያና ፍትሕ ማስፈኛ እሴት ከመደበኛ የሕግ ሥነ ሥርዓት ጋር በማይጋጭ መልኩ በመቃኘት በቅርበት አገልግሎት እየሰጡ ናቸው ሲሉ ጠቁመዋል።
የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በቀጣይ የዳኝነት ሥርዓቱን የማስፋፋት ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል።
ከተጠቃሚዎች መካከል የሺሺንዳ ከተማ ነዋሪ አቶ ካሳሁን ማሞ መንግስት የፈጠረልን በባህላዊ መንገድ የመዳኘት ምቹ ሁኔታ ፍትሕን ያለ ድካም በቅርበት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል።
በባህላዊ ፍርድ ቤት ሲያደርጉት ለነበረው ክርክር ተገቢውን ውሳኔ ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።