ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተካሄዱ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ ሆነናል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተካሄዱ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ ሆነናል
ከሚሴ፤ ሐምሌ 14/2018(ኢዜአ)፡-ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ በተደረጉ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በከሚሴ ከተማ "የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደር ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው ስለ ኢትዮጵያ የተሰኘ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የከሚሴ ከተማ ነዋሪ ሼህ የሱፍ ይማም እንደገለፁት፣ በለውጡ ዓመታት በተቀናጀ መንገድ ሰላምን ከማስፈን ባሻገር ተግባራዊ በተደረጉ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ ሆነናል።
ከለውጡ በፊት ከተማዋ በልማት ወደ ኋላ የቀረች ከመሆኑ በተጨማሪ ግጭቶች የሚታዩባት እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ የተሟላ ሰላም ከመሰፈኑ ባሻገር በከተማዋ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች መሟላታቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የባቲ ከተማ ነዋሪ አቶ ኡመር መሐመድ በበኩላቸው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚሰሩ የልማት ስራዎች ማሕበረሰቡ ለረዥም ጊዜ ሲያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ናቸው።
በተለይም የአካባቢውን ሰላም ከማጽናት ባለፈ የዲጂታል አገልግሎት በተሻለ ጥራት ተደራሽ በማድረግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
የአካባቢያችን ሰላም ተጠብቆ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ ሆነናል ያሉት ደግሞ የጨፋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ አቶ አሊ ሰይድ ናቸው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከአጎራባች ዞኖችና ክልሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በማጠናከር በልማት ጭምር መተሳሰሩ ይበልጥ እንድንቀራረብና በጋራ ተጠቃሚ መሆን እንድችል አድርጓል ነው ያሉት።
የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰላምን ለማስፈን በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት ።
ከሰላም ማስክበር ስራው በተጓዳኝ የህዝቡን የልማት ጥያቄ መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎችን በማከናወን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደተቻለ ገልፀዋል።
በመድረኩ የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ የፌዴራል ፣ የክልል ፣ የዞንና የከተማ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።