ቀጥታ፡

በዞኑ ህብረተሰቡን በቅርበት ለማገልገል ወደ ተግባር የገቡ የቀበሌ አደረጃጀቶች ለልማት ስራዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል

ጊምቢ፣ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፡-በምዕራብ ወለጋ ዞን ህብረተሰቡን በቅርበት ለማገልገል ወደ ተግባር የገቡ የቀበሌ አደረጃጀቶች የተሟላ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ለልማት ስራዎች ምቹ ሁኔታ እንደፈጠሩላቸው ነዋሪዎች ገለጹ።

አደረጃጀቱ በቅርበት የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ፣ ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳድጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ እንደሚገኝ  የዞኑ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት ነዋሪዎች መካከል የጊምቢ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አስካለ ሕርጳ፤ የቀበሌ አደረጃጀቱ የመንግሥት አገልግሎትን በቅርበት ከማግኘታቸው በላይ በአካባቢያቸው የተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ አስችሏል፡፡

በተለይም አደረጃጀቱ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በአካባቢያቸው የነበረውን የጸጥታ ችግር መቅረፍ መቻሉን ጠቅሰው፤ አመራሮቹ በየጊዜው ከህብረተሰቡ ጋር በመቀራረብ ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የመንዲ ከተማ የቀርሳ ዋልጋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ በላይ መልካሙ በበኩላቸው፣ የተዘረጋው አደረጃጀት ተጠቃሚነታቸውን ያሳደጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።

በተለይም በአካባቢያቸው ሰላም እንዲሰፍን ከማድረጉም በላይ የቆዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

አሁን የተዘረጋው የቀበሌ አደረጃጀት ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ወደተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከማመልከትና ከመንገላታት እንደታደጋቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ አያና ገላልቻ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ከመሬት ወሰን ይዞታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ለተለያዩ እንግልቶች ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ ማስፈጸም መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

አደረጃጀቱ በስራ ላይ መዋሉ ውስብስብ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታትና ሠላም እንዲሰፍን በማድረግ በኩል አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

የቀበሌ አደረጃጀቱ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለህብረተሰቡ በቅርበት መስጠት ማስቻሉን የተናገሩት ደግሞ የጊምቢ ከተማ 01 ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ሙሊጌታ አደሙ ናቸው።

በአደረጃጀቱ ህብረተሰቡን በማቀናጀት በአካባቢው የነበረውን የጸጥታ ችግር በመቅረፍ ሰላም እንዲሰፍን ተድርጓል ብለዋል።

በቀጣይም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየትና ተደራሽ የሆኑ አገልግሎቶችን በማሳለጥ የህዝብ ጥያቄዎችን አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰራ አመላክተዋል።


 

የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፋ እንደተናገሩት በዞኑ 464 የቀበሌ አደረጃጀቶች ተደራጅተው ለሕዝቡ በቅርበት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።

አደረጃጀቱ በተለይም በዞኑ ይስተዋሉ የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በመቅረፍ ሂደት ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር እንዲሰራ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የዞኑ ህዝብ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳቸው የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ፈጥኖ ለመመለስ እድል መፍጠሩንም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም