ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ለዓለም ያበረከተችው ታሪካዊ ዕሴት በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ለዓለም ያበረከተችው ታሪካዊ ዕሴት በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን የዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ሕብረት (IUCN) የዝርያዎች ሕልውና ኮሚሽን ሊቀመንበር ቪቬክ ሜኖን (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል "60 ዓመታትን ለኢትዮጵያ የዱር ሕይወት" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን የቦርድ ሰብሳቢ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ሕብረት (IUCN) የዝርያዎች ሕልውና ኮሚሽን ሊቀመንበር ቪቬክ ሜኖን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ታሪካዊ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ባህልና ቅርስ በአርዓያነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ታሪክ ጥቂት አሥርተ ዓመታትን ብቻ ሳይሆን በርካታ ክፍለ ዘመናትን ወደ ኋላ የሚመልስ ጥንታዊ መሠረት ያለው መሆኑን አስታውቀዋል። 

ኢትዮጵያ ገና በ15ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ አፄ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የመናገሻ ደንን በመጠበቅና በማወጅ የተፈጥሮ ሀብቷን መንከባከብ የጀመረች ሀገር መሆኗን አንስተዋል። 

ይህም እርምጃ ደኖችና ተፈጥሮ ለዓለም ሕልውና ያላቸውን ከፍተኛ አስፈላጊነት ቀድማ ያወቀችና ጥንታዊ የነቃ አስተዳደርነትን ያሳየች ሀገር መሆኗን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም ተፈጥሮዋን ለማስጠበቅ እያደረገች ያለችው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስታውቀዋል።

የዱር እንስሳትና ብዝኃ ሕይወት ከሥነ-ምህዳር ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ያለ ዝርያዎች ሕልውናና ያለ ብዝኃ ሕይወትሥነ-ምህዳርን በብቸኝነት መጠበቅ እንደማይቻል አስገንዝበዋል። 

አብዛኞቹ የዓለማችን ድንቅ ፍጥረታት የሚገኙት በምሥራቁ የዓለም ክፍል፣ በተለይም በአፍሪካ እና በእስያ አህጉራት በመሆኑ ዓለም የነዚህን አህጉራት ተፈጥሮ የመጠበቅና የመንከባከብ ከፍተኛ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።

የIUCN የዝርያዎች ሕልውና ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከ12,000 በላይ ገለልተኛ ሳይንቲስቶችንና ባለሙያዎችን በአባልነት አቅፎ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም