ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እያበረከተችው ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እያበረከተችው ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እያበረከተችው ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የብዝሃ ሕይወት ስምምነት (CBD) አስፈጻሚ ጸሀፊ አስትሪድ ሾማከር ገለጹ።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው፡፡
በመድረኩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን የቦርድ ሰብሳቢ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የብዝሃ ሕይወት ስምምነት (CBD) አስፈጻሚ ጸሀፊ አስትሪድ ሾማከር ፣ ኢትዮጵያ የበርካታ፣ ልዩ የእፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች መገኛና የብዝሃ ሕይወት ማዕከል መሆኗን ተናግረዋል።
ሀገሪቱ ለዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እያበረከተች ያለው ሚና እጅግ ጉልህ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በሌላ ቦታ የማይገኙ ብርቅዬ ዝርያዎች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህ ልዩ የተፈጥሮ ቅርስ ለኢትዮጵያ ኩራት ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ሊተመን የማይችል እሴት እንዳለው ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የተፈጥሮና የብዝሃ ሕይወት ቅርሶችን ለመጠበቅ ተቋሙ ላሳየው ቁርጠኝነትም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ሀገሪቱ የጥበቃ ቦታዎችን በሚገባ በማስተዳደር፣ አደጋ ላይ ያሉ ዝርያዎችን በመታደግ እና በሰውና በዱር እንስሳት መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመቆጣጠር ያደረገችው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አብራርተዋል።
የተቀመጡ የብዝሃ ሕይወት ግቦችን ስኬታማ ለማድረግ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የደን ሀብትን በመጠበቅ፣ ዝርያዎችን ከአደጋ ለመታደግ እና ሕገወጥ የዱር እንስሳት ንግድን ለመቆጣጠር የተፋጠነ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል።