ቀጥታ፡

ባለሥልጣኑ የዱር እንስሳት ሀብትን በዘላቂነት ለመንከባከብና ዓለምአቀፍ ትብብርን ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የዝርያ ጥበቃን ለማጠናከር፣ የዱር እንስሳት ሀብትን በዘላቂነት ለመንከባከብና ዓለምአቀፍ ትብብርን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ለአደጋ የተጋለጡ የዱር አራዊትና ዕፅዋት ዝርያዎች ዓለምአቀፍ ንግድ ስምምነት (CITES) ዋና ፀሐፊ ኢቮን ሂጌሮ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "60 ዓመታትን ለኢትዮጵያ የዱር ሕይወት" በሚል መሪ ሀሳብ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ፣ እንዲሁም አምባሳደሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

ለአደጋ የተጋለጡ የዱር አራዊትና ዕፅዋት ዝርያዎች ዓለም አቀፍ ንግድ ስምምነት (CITES) ዋና ፀሐፊ ኢቮን ሂጌሮ በዚሁ ወቅት፤ ባለሥልጣኑ ባለፉት ዓመታት የዝርያዎች ጥበቃን ለማጠናከር፣ ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድን ለመከላከልና ዓለም አቀፍ ትብብርን ማሳደግ ያስቻሉ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1989 ስምምነቱን ከተቀላቀለችበት ጊዜ ጀምሮ ከሴክሬተሪያቱ ጋር ላላት የረጅም ጊዜ አጋርነት ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ፣ በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ እና በሌሎችም መሠረተ-ልማቶች በሚገኙ የክትትል ጣቢያዎች በኩል ዝሆኖችን ለመቆጣጠር የሚረዳ ጠቃሚ መረጃን ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲያካፍል ቆይቷል ብለዋል።

እነዚህ ስኬቶች የባለሥልጣኑ ሠራተኞች፣ ሬንጀሮችና የአካባቢው ማኅበረሰብ አጋሮች ከአፍሪካ ዝሆን እስከ ጭላዳ ባቡን እና ብርቅዬ እንስሳት ጥበቃ ያደረጉት የማያቋርጥ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ትብብር እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም