ቀጥታ፡

የአረንጓዴ ዐሻራ የሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን በመጠበቅ የዱር ሕይወት መጠጊያና መኖሪያ የሚያገኙበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን በመጠበቅ የዱር ሕይወት መጠጊያና መኖሪያ የሚያገኙበትን ወሳኝ ዕድል መፍጠሩን የኢፌድሪ ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል "60 ዓመታትን ለኢትዮጵያ የዱር ሕይወት" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት ያከማቸችውን የዱር ሕይወት ጥበቃ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር ከአፍሪካ ግንባር ቀደም እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያውያን የዱር ሕይወት ጥበቃ ባህላዊ ሥርዓትም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ አስደናቂ ዕሴት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት መለያ የሆነው የዋሊያ አይቤክስ መመናመን አሳሳቢ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህንን ለመታደግ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታ አለብን ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በአጉል ልማድና ኋላ ቀር አስተሳሰብ በመነሳት በዱር እንስሳት ላይ የሚደርሰውን ጥፋት በማስቆም ጸጋዎችን አጥብቆ መያዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተፈጥሮ ሀብቶችንና የብዝኃ ሕይወት ሥነ-ምህዳር ሚዛንን ለመጠበቅ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም የደረቁ ምንጮችንና ደኖችን በመመለስ ሸሽተውና ጠፍተው የነበሩ የዱር እንስሳት መጠጊያና መኖሪያነት እያገለገሉ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ የታየ እውነታ መሆኑን በማንሳት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሁለንተናዊ ስኬት እንዲመዘገብ በማስቻል ለብዝኃ ሕይወት ደኅንነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

ቀደም ሲል ከነበረው ልማዳዊ አሠራር ሰንሰለት በመላቀቅ በብሔራዊ ፓርኮች ልማት አዲስ ሕይወትና እይታ ለመስጠት የተደረገው ርብርብ ትልቅ እመርታ ማምጣቱንም ጠቁመዋል።

የፓርኮችን ደኅንነት ማረጋገጥ እና መሠረተ ልማቶቻቸውን ማዘመን ለዱር ሕይወት ጥበቃ ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ ለሚደረገው ጥረት ቁልፍ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በከተሞች እየተገነቡ ያሉ ፓርኮችም ሕብረተሰቡ ለዱር ሕይወት ያለውን የእውቀት አድማስ የሚያሰፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት ተግቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ባለፉት ስልሳ ዓመታት ባለሥልጣኑ እንዲሁም አጋር አካላት ተፈጥሮን ለመጠበቅ ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን የቦርድ ሰብሳቢ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም