ልማትና ዴሞክራሲን ጎን ለጎን በማስኬድ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ልማትና ዴሞክራሲን ጎን ለጎን በማስኬድ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ)፦ ልማትና ዴሞክራሲን ጎን ለጎን በማስኬድ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ የብሔራዊነት ገዥ ትርክትን ማስረጽና ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህን ጨምሮ የዋና ጽህፈት ቤት የዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች አመራሮች እየተሳተፉ ናቸው።
አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ እንደገለፁት ልማትና ዴሞክራሲን ጎን ለጎን በማስኬድ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
የ2018 በጀት ዓመት በተቋም ግንባታ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት እና በልማት ሥራዎች ጉልህ ውጤቶች የተመዘገቡበት ዓመት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በጀት ዓመቱ ከፓርቲ ግንባታ አኳያ ብልፅግና በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ በሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት እንዲሁም በማስፈጸም አቅሙ ተጠናክሮ የወጣበት ዓመት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ድርብርብ ተልዕኮዎችን በታቀደው መሰረት ማሳካት የተቻለበት በጀት ዓመት ነው ብለዋል።
መላው ህዝብ በእያንዳንዱ ተልዕኮ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ በመደረጉና በባለቤትነት ስሜት ከብልፅግና ፓርቲ ጎን በመቆሙ፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጠንካራ መሰረት የጣለውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ መንታ ግቦች በላቀ አፈጻጸም ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።
ልማትና ዴሞክራሲን ጎን ለጎን በማስኬድ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት የላቀ ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል።
አክለውም የፓርቲውን ግዙፍ አቅም አሟጦ በመጠቀምና የአመራር ሥነ-ምግባር ልህቀትን በማረጋገጥ የሕዝብን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአመራርና አባላትን ጥራት ማረጋገጥ፣ የብሔራዊነት ገዥ ትርክትን ማስረፅ እና የፓርቲውን ተቋማዊ የማዕቀፍ ስታንዳርድ (Standardization) የመገንባት ሥራ በተጠናከረ መንገድ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ለዚህም የአመራሩ፣ የአባላቱና የመላው ሕዝብ ርብርብ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ፤ በ2018 ዓ.ም የአፈጻጸም ሪፖርት እና በ2019 ዓ.ም መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን፣ የቀጣይ አቅጣጫዎችም ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።