ቀጥታ፡

የተፈጥሮ ሀብትና የዱር እንስሳት ጥበቃ ሥራዎች ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያልቁ ተግባራት ይጠናከራሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018(ኢዜአ)፦ የተፈጥሮ ሀብትና የዱር እንስሳት ጥበቃ ሥራዎች ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያጎሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል፡፡

በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመሩት የገበታ ለሀገር፣ የገበታ ለሸገር እና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ለቱሪዝም ዘርፉ አዳዲስ ምዕራፎች መክፈታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የዱር እንስሳት እንዲመለሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ላይ ትውልዱ አደራውን በሚገባ እንዲወጣ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ የዱር እንስሳት፣ በብርቅዬ የተፈጥሮ ሀብቶችና በውብ ስነ-ምዳሮች የበለፀገች ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ እነዚህን ጸጋዎች ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም የጋራ አደራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለተፈጥሮ ሀብት እና ለዱር እንስሳት ጥበቃ በሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት የሀገሪቱን የደን ሽፋን ማሳደግ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

የቱሪዝም እድገት ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተፈጥሮ ሀብትና የዱር እንስሳት ጥበቃ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ባለፉት 60 ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጉዞ በብዙ ውጣ ውረዶች ያለፈ መሆኑን ጠቅሰው ለዘርፉ ዕድገትና ለዱር እንስሳት ጥበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም