የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማትን በማጠናከር ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማትን በማጠናከር ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማትን በማጠናከር ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በዚሁ ወቅት፤ ተፈጥሮ ለኛ ከተሰጠ ሀብትነት ባሻገር ለመጭው ትውልድ የምናስተላልፈው አደራ ጭምር ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው ተራሮች፣ ሰፋፊ ወንዞች፣ ረግረጋማ ቦታዎች፣ ጥልቅ ሸለቆዎች እና ሀይቆች የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ሀብት መለያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዋልያ አይቤክስ፣ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ እንዲሁም በርካታ አእዋፋትና አበቦች በተፈጥሮ ሀብታችን የታደልናቸው የሀገራችን ማንነት እና የኢኮኖሚያችን አቅም ናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የዱር ህይወት ጥበቃ በኢትዮጵያ ከዘመናዊ ተቋማዊ አደረጃጀት በፊት በባህላዊና ማህበራዊ እሴቶቻችን ውስጥ ዘመን የተሻገረ፣ ስር የሰደደ እና የማህበረሰብ ጥበቃ ተሞክሮዎች ለዛሬው ጥበቃ መሰረቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከ60 ዓመታት በፊት በሁለት ብሔራዊ ፓርኮች የተጀመረው ዘመናዊ የጥበቃ ጉዞ፣ ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ከ30 በላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
በርካታ የዱር እንስሳት መጠለያዎች ከ106 በላይ ልዩ ልዩ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
ዛሬ እንደ ሰፊ የጥበቃ ቦታዎች አስተዳደር፣ የብሔራዊ ፓርኮች ልማት፣ የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ፣ ዘላቂ ቱሪዝም እና የማህበረሰብ ተሳታፊነት የተመሰረተበትን ልማት ማረጋገጥ መቻሉን አመላክተዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጥበቃ ቦታዎች አስተዳደር እንዲጠናከር፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳታፊነት እንዲያድግ፣ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች እንዲሻሻሉ እና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በጥበቃ ስራ ውስጥ በስፋት እንዲተገበሩ መደረጉን አንስተዋል፡፡
ዛሬ የምናከብረው 60 ዓመታት የቆየ ተስፋ፣ 60 ዓመታት የተከፈለ መስዋዕትነት፣ 60 ዓመታት የተጻፈ ታሪክ፣ እና 60 ዓመታት ለቀጣዩ ትውልድ የተሸከምነው አደራ ነው ብለዋል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀም፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ዋና ተጠቃሚና ባለቤት ማድረግ፣ ከአጋር ተቋማት ጋር ያለንን ትብብር ማጠናከር፣ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምሮችን ማጎልበት የወደፊት የጥበቃ ስራዎቻችን መሰረታዊ አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡