በክልሉ የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመቋቋም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመቋቋም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦በአማራ ክልል የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመቋቋም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን ተግባራዊ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለግብርና ልማት ምርታማነትና የአየር ጸባይ ለውጥን መከላከል ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በመሆኑም በክረምቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ1 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ነው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅትም በበጋው ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተከናወኑባቸው ቦታዎችና ሌሎች አካባቢዎች ጥምር ጥቅም የሚሰጡ ችግኖች እየተተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።
የችግኝ ተከላ ስራው የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ባለፈ የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንፃር የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል።
ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተካሄደ በሚገኘውን የችግኝ ተከላ ከማሳካት ጎን ለጎን ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ የጽድቀት መጠኑን ለማሳደግ እንደሚሰራም አብራርተዋል።
በአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ አንጓይ ቀበሌ አርሶ አደር ስሜነህ አያል እንደገለጹት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ለእንስሳት ግጦሽ መስፋፋትና ለመኖ ልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ።
በወተት ልማት፣ በንብ ማነብና በከብት ማድለብ ስራ ያረጋገጡትን ተጠቃሚነት ለማሳደግም በችግኝ ተከላ ስራ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዚሁ ወረዳ የብዝራካኒ ቀበሌ አርሶ አደር መኮንን ፈንታው፣ የችግኝ ተከላ የአፈር ለምነትን በመጨመር ለግጦሽ መሬት ልማት እንዳገዛቸው አስረድተዋል።