ቀጥታ፡

በምእራብ ጎንደር ዞን ከ22 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል

ገንዳውኃ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ22 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የዞኑ ሥራና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።  

​የመምሪያ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር በማቃለል በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።

​በዚህም በበጀት ዓመቱ በዞኑ የሚገኙ ጸጋዎችን በመለየት ከ22 ሺህ 500 በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ  የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በኮንስትራክሽን፣ በእንጨትና ብረታ ብረት ስራ፣ በአገልግሎት ፣ በከብት ማድለብ፣ በወተት ልማትና ንብ ማነብን ጨምሮ በሌሎች የግብርና ዘርፎች መሰማራታቸውን ገልፀዋል።

የስራ እድሉ የተፈጠረላቸው ዜጎች  267 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የመስሪያ ካፒታል በብድር እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈም ለማምረቻና ለመሸጫ የሚሆኑ ከ700 በላይ ሼዶችና ኮንቲነሮችን ማስረከብ መቻሉን አስረድተዋል።

በቀጣይም የዞኑን እምቅ ጸጋዎች በሚገባ ለይቶ በመጠቀም ለወጣቱ የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።

​በዞኑ በከብት ማድለብ ስራ የተሰማራው ወጣት ይስማው አቡዬ ፤በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተመቻቸለት የከብት ማድለብ ሥራ ከ300 ሺህ ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘት መቻሉን ነው የተናገረው።

በዚህም ከራሱ አልፎ ቤተሰቦቹን ለመደገፍ እንደቻለ አመልክቶ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በዘላቂ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በእጣንና ሙጫ ማምረት ስራ የተሰማራው ወጣት አይሸሽም አለሙ በበኩሉ፤  ከ100 ባለይ ሆነው በመደራጀት በዘርፉ ባገኙት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል።

በበጀት ዓመቱ እጣንና ሙጫ በማምረትና ለገበያ በማቅረብ እያንዳንዳቸው ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ነው ያስታወቀው።

በአሁኑ ወቅትም  የተፈጥሮ ደኑ እንዲጠበቅ በጋራ ሆነው እየሰሩ መሆኑንም አመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም