ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች - አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር እና የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት የኦስትሪያ አምባሳደር ገለጹ።

ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የምትከተላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ዓለም አቀፍ ትኩረት እየሳቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያን እየተገበረች እና ዲጂታል ሥርዓትን እያስፋፋች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር እና ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር ለመቀናጀት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በርካታ የእስራኤል ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲና በዲጂታል ሥርዓት እየተሳቡ እንደሚገኙ የገለጹት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ በኃይል፣ በውሃ እና በሌሎችም ቁልፍ ዘርፎች ባላት ፖሊሲ ትክክለኛ የልማት አቅጣጫዎች ላይ እየተጓዘች መሆኑን አረጋግጠዋል። 

የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ተደራሽነት ማስፋፋትን ጨምሮ ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት እያሳየች ያለው እመርታዊ ለውጥ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያጠናክር መሆኑንም ተናግረዋል።

ሀገራቱ በግብርና፣ በጤና፣ በፈጠራና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት እና በምርምር ዘርፎች ላይ የጋራ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወናቸውን አብራርተዋል። 

በማህበራዊና ሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ረገድም ሀገራቱ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው ያነሱት አምባሳደሩ፤ በጤና፣ በባህል ልውውጥ፣ በንግድ ትስስር እና በቱሪዝም ዙሪያ ያላቸውን ግንኙነት በማሳያነት አንስተዋል። 

እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እያጠኑ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም በጠብታ መስኖ፣ በሰብል ምርት፣ በአቮካዶ፣ ስንዴ፣ ዓሣ እና የዶሮ እርባታ ባሉ የግብርና ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕ  (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርም የኦስትሪያ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ እንዲያማትሩ እና አማራጮችን እንዲመለከቱ እያደረገ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማድረግ የጀመረችው ጉዞ በትክክለኛ የዕድገት ጎዳና ላይ እንድትቀመጥ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ በተጨባጭ ኢንቨስት እያደረጉ ያሉ የኦስትሪያ ኩባንያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህንን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የያዘችው ትክክለኛ የልማት ጎዳና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችን እየሳበ በመሆኑ ማሻሻያው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የኢኮኖሚ ተሳትፎ፣ የትምህርት ትብብር እና የባህል ልውውጥን ጨምሮ የሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚጠናከርም ጠቁመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም