ከተሞችን ለኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም የተመቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞችን ለኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም የተመቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ከሚሴ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ ከተሞችን ለኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም የተመቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በከሚሴ ከተማ "የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደር ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው ስለ ኢትዮጵያ የተሰኘ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፣ የከተሞችን ፈጣን እድገት በማስቀጠል ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው።
የከተሞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ፈጣንና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት በመስጠት ላይ ተመስርቶ እየተካሔደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይ በኮሪደር ልማት፣ በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በዲጂታላይዜሽንና የስማርት ሲቲ ትግበራ ከተሞችን ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝምና ንግድ ተመራጭ የማድረግ ስራ ትኩረት የተሰጠው ነው ብለዋል።
ይህም ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር፣ በእውቀት ሽግግርና ልምድ በመቅሰም ኢትዮጵያ በአስተማማኝ የእድገት መሰረት ላይ እንድትጓዝ የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።
በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለልም በመንግስት፣ በማህበርና በባለሃብቶች የተጀመረው የቤት ግንባታ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ይህም ከፍተኛ መነቃቃትና ተስፋ ከመፍጠሩ ባለፈ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው፣ በዞኑ የሚገኙ ከተሞችን በኮሪደር ልማትና በሌሎችም መሰረት ልማቶች ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ይህም አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራሮችን እንዲያጠናክር ከማድረጉም በላይ የዞኑን ሰላም በመጠበቅ በኩል ለውጥ ማስገኘቱን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጀመራቸው መድረኮች ከተሞችን ከማነቃቃት ባለፈ በሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ላይ መወያየት እንዲቻል ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
በምክክሩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራሮች፣ አባ ገዳዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።