እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ አለው - ኢዜአ አማርኛ
እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ አለው
ሆሳዕና፤ ሐምሌ 14/2018(ኢዜአ)፦ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከህዝብ የሰበሰባቸውን አጀንዳዎች ለይቶ እና አደራጅቶ ለምክክሩ ይፋ ባደረጋቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር እየተካሄደ ይገኛል።
የምክክር ሂደቱ የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች በማከም የጸናችና ለትውልዱ የምትመች ሀገር ለመገንባት ጠንካራ መሰረት ለማኖር ያስችላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሐምሌ 8/2018 ዓም በምክክር ጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በምክክሩ ከየሰፈራችን ወጥተን ለኢትዮጵያ ስንመክር፣ ለልጆቻችን ስንልና እነርሱን እያሰብን ስንወያይ ውጤቱ ፍሬያማ ይሆናል ማለታቸው ይታወቃል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን እንዳሉት እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ደህንነት ጥናት መምህርና ተመራማሪ ተመስገን ቶማስ (ዶ/ር) አሁን እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ለጋራ ተጠቃሚነት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የሀገር እድገትና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ጠቁመው ጎታች አመለካከቶችን በሀገራዊ ምክክሩ በመፍታት ለጋራ ተጠቃሚነት መስራት ይገባል ነው ያሉት።
ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መምከር ለቆዩ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ማምጣትና የተዛቡ ትርክቶችን ማረም እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።
እየተካሔደ ያለውን ሀገራዊ ምክክር በአግባቡ በመጠቀም ለሀገር እድገትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የምክክር ሂደቱ ለቆዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄን ይዞ ከመምጣቱ ባለፈ የህዝቦችን አብሮነት በማጠናከር የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያጠናክር ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አበራ ሄቢሶ ናቸው።
ለዚህም በኮሚሽኑ ተለይተው የቀረቡ አጀንዳዎች ለቆዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትና ለተተኪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስተላለፍ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ሲሉ ገልጸዋል።
የሚነሱ ችግሮችን በማረም ለሀገረ መንግስት ግንባታው መጠናከር የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።