ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን በበልግ ወቅት ከለማው መሬት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል

ደሴ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦በደቡብ ወሎ ዞን በበልግ ወቅት የእርሻ ስራ ከለማው መሬት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ በዞኑ በመኸር፣ በመስኖና በልግ ሰብል ልማት አርሶ አደሩን በንቃት በማሳተፍ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ጥረት እየተደረገ ነው።

በዚሁ ወቅት ከ104 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ቦሎቄ ፣ ማሾ ፣ ጤፍ ፣ ስንዴ ፣ ሽምብራና ምስር ሰብሎችን ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።

ምርታማነቱን ለማሳደግም ግብአትን በአግባቡ በመጠቀምና ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

በበልግ ሰብል ልማት ከተገኘው ምርት በተጨማሪ ተረፈ ምርቱን ለእንስሳት መኖነት በመጠቀም የወተትና የስጋ ምርትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።

የበልግ ዝናቡ ለሰብል ልማት ምቹ እንደነበር አውስተው አሁን ላይ ሰብሉን ቀድሞ በማንሳት ለመኸር ሰብል ልማት ዝግጁ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በዞኑ አርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ የ07 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የሱፍ አህመድ እንዳሉት፣ በዘንድሮው የበልግ ዝናብ ከአንድ ሄክታር መሬት በላይ ማሾና ቦሎቄ ማልማት ችለዋል።

ካለሙት መሬት ላይም 12 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ጠቁመው ከፍጆታ የተረፈውን በመሸጥ ጥሪት ለማፍራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የተሁለደሬ ወረዳ 013 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኢብራሂም ደምስ በበኩላቸው፣ በበልግ ዝናብ ካለሙት አንድ ሄክታር መሬት የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከእለት ፍጆታ የተረፈውን ምርትም ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም