ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን የሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋን በራስ አቅም ለመቋቋም ርብርብ እየተደረገ ነው

ደብረ ማርቆስ ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦በምስራቅ ጎጃም ዞን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን  በራስ አቅም ለመቋቋምና በምግብ ራስን ለመቻል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አደጋ መከላከልና ስራ አመራር ተጠሪ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሾመ መኮነን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በምግብ ራስን ለመቻል መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ በማድረግ በኩል ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ  ይገኛል።

በተለይም በአካባቢው ዝናብ አጠር ፣ ጎርፍና በረዷማ በሆኑ ወረዳዎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲገጥም በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም በተያዘው የክረምት ወቅት ከሁለት ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት የሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮችን  በራስ አቅም ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሁሉም ወረዳዎች ከ400 ሄክታር በላይ መሬት ደጋግሞ የታረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 40 ሄክታር የሚሆነውን በስንዴና በጤፍ ዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።

ከዚህም  ከ96 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ነው ያስረዱት።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም ከሰባት ሺህ 500 ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በማሰራጨት አርሶ አደሩ ጥቅም ላይ እንዲያውለው መደረጉን አብራርተዋል።

የደጀን ወረዳ የየትኑራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መኩሪያው ፈለቀ፤ ከተረጅነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ  የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀበሌያቸውም  በምግብ  ራስን ለመቻል የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በመሳተፍ ለዚሁ የተዘጋጀውን መሬት የማረስ ስራ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ገልፀዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ነገሰ ኑሬ በበኩላቸው ፤በቡድን በመሆን በምግብ ራስን ለመቻል የተለየውን መሬት በማረስ ለዘር ዝግጁ አድርገው እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀዋል ።

ማሳውን በዘር ከመሸፈን ባለፈ በአረም፣ ሰብሉን ከተባይ በመከላከልና ከመንከባከብ ጀምሮ እስከ ሰብል ስብሰባው ድረስ በመሳተፍ ድርሻቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል።

በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በምግብ ራስን ለመቻል በተደረገው እንቅስቃሴ ከ104 ሚሊዮን ብር  በላይ ከማህበረሰቡ በማሰባሰብ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን ከተጠሪ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም