የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ17 አደገኛ የወንጀል ቡድን አባላት የምርመራ መዝገብ ለፍትሕ ሚኒስቴር ላከ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ17 አደገኛ የወንጀል ቡድን አባላት የምርመራ መዝገብ ለፍትሕ ሚኒስቴር ላከ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2018 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ17 አደገኛ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ የምርመራ መዝገብ በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማደራጀት ለፍትሕ ሚኒስቴር መላኩን አስታወቀ።
ፖሊስ እንደገለጸው በምሥራቅ ሀገራችን በኩል በጂቡቲ እና በየመን አድርገው ወደ ሳውዲ አረቢያ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ሲልኩ የቆዩና ከተጎጂዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተቀበሉ፣ በአደገኛ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪ መሐመድ ጣሂር አደን (ወርዲ) የሚመሩ የተደራጁ 17 የወንጀል ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር አውሎ የምርመራ መዝገብ በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማደራጀት ለፍትሕ ሚኒስቴር ልኳል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባሰባሰበው የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ተጠርጣሪዎቹ በሰው ልጅ ለመነገድ በማሰብ የወንጀል ቡድን በማደራጀት በወንጀል ድርጊቱ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ መሳተፋቸውን በምርመራ መዝገቡ ማጣራቱን ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ በመዘርጋት፣ ተጎጂዎቹ በየመን በኩል ወደ ሳውዲ አረቢያ ገብተው የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩ ሐሰተኛ ተስፋ በመስጠትና በማሳመን ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በደላሎች አማካኝነት ተጎጂዎችን በመመልመል ሲልኩ መቆየታቸውንም ፖሊስ አረጋግጧል።
በምርመራ መዝገቡ እንደተመለከተው በሕገ-ወጥ መንገድ የተወሰዱ ተጎጂዎች የኢትዮጵያን ድንበር እንደተሻገሩ ወደ የመን ተወስደው በየመን ሀገር ውስጥ በሚገኙ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጁ መጋዘኖች ታጉረው ከፍተኛ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸው ነበር።
በተለይም ተጠርጣሪዎቹ ተጎጂዎችን በመያዣነት በመያዝ ወደ ቤተሰቦቻቸው ስልክ በማስደወል ከፍተኛ ገንዘብ ሲጠይቁ እንደነበር እና ገንዘብ መክፈል ላልቻሉ ቤተሰቦች ተጎጂዎችን እየደበደቡ እንዲሁም እያሰቃዩ ቪዲዮ በመቅረጽ የሥነልቦና ጫና ሲፈጥሩ እንደነበር ፖሊስ አረጋግጧል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ባደረገው ጠንካራ ክትትልና ምርመራ በርካታ ከባባድ ግኝቶችን ይፋ አድርጓል።
ከእነዚህም መካከል ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ከተጎጂዎች ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ መቀበላቸውን፣ ከ40,000 በላይ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወራቸውን፣ ከ60 ሰዎች በላይ ለሕልፈተ ህይወት መዳረጋቸው እንዲሁም በርካታ ሴቶች መደፈራቸው በምርመራ ተደርሶባቸዋል።
በዚህ ወንጀል ጉዳይ በርካታ ሰዎች የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ከሳውዲ አረቢያ እና ከኢትዮጵያ በቀጥታ መስመር በቪዲዮ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በሕገ-ወጥ መንገድ ያገኙትን ከፍተኛ ገንዘብ በመጠቀም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ማፍራታቸውን ፖሊስ ያረጋገጠ ሲሆን በስማቸው የነበረ ቤት፣ ተሽከርካሪ እና ገንዘብ እንዲታገድ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በሰው የመነገድ፣ በሕገወጥ ሀዋላ እና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር (Money Laundering) ወንጀሎች ምርመራውን አጠናቆ ለፍትሕ ሚኒስቴር መላኩን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናውን እያቀረበ፤ ኅብረተሰቡ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፣ 991 ነፃ የስልክ መስመር እና ሰው አልባ ፖሊስ ጣቢያ (SPS)ን በመጠቀም መረጃ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል።